የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ከክልሉ መንግስት ጋር “አብሮ ለመስራት” ያሳለፈውን ውሳኔ እንደገና ለማጤን መገደዱን ገለጸ

በናሆም አየለ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ)፤ ከክልሉ መንግስት ጋር “አብሮ ለመስራት” ያሳለፈውን ውሳኔ እንደገና እንደሚያጤነው ገለጸ። ፓርቲው አብሮ የመስራቱን ሂደት ለማጤን የተገደደው በአባላቱ፣ በደጋፊዎቹ እና አመራሮቹ  ላይ “ እስር፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ” እየደረሰባቸው በመሆኑ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።

ቦዴፓ ትላንት ማክሰኞ መስከረም 7፤ 2017 ባወጣው መግለጫ፤ ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተደረገው ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ በኋላ በክልሉ “የዴሞክራሲ ምህዳር መጥበቡን” ጠቅሷል። ፓርቲው በዚሁ ምርጫ  ሶስት የክልል ምክር ቤት እና አንድ የፓርላማ መቀመጫ በቡለን ወረዳ እና ሽናሻ ልዩ ምርጫ ክልሎች ላይ አሸንፏል።

ፓርቲው ለክልል እና ለፌደራል ምክር ቤቶች በተወዳደረባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ አባላቱ፣ ደጋፊዎቹ እና አመራሮቹ ላይ “የተቀናጀ ወከባ፣ እስራት፣ ድብደባ፣ ህገወጥ የስራ ዝውውር፣ መብት እና ጥቅም በመንፈግ” እየደረሰ እንደሚገኝም በመግለጫው ዘርዝሯል። ቦዴፓ “የፖለቲካ አመለካከትን መሰረት ያደረገ ጫና እያደረሱብኝ ነው” ሲል  በመግለጫው የወነጀላቸው፤ በክልሉ ያሉ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አመራሮችን ነው። 

ቦዴፓ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሰው ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ በቡለን ከተማ የተካሄደን ስብሰባ ነው። በስብሰባው ላይ ከወምበራ፣ ድባጤ እና ቡለን ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች መገኘታቸውን የጠቀሰው የፓርቲው መግለጫ፤ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች “ለምን የቦዴፓ እጩዎችን መረጣችሁ?” በማለት ከፍተኛ “ዛቻ፣ ማስፈራሪያ እና ስድብ” መሰንዘራቸውን አመልክቷል። 

“[ከፍተኛ አመራሮቹ] የህዝብ ድምጽ ያገኙ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ‘በእስር ቤት እናጉራችኋለን’ በማለት፤ ፍጹም አምባገነናዊ እና ኋላ ቀር አቋማቸውን በግልጽ የህዝብ መድረክ ላይ አራምደዋል” ሲል ቦዴፓ ተችቷል። ድርጊቱንም “ለህዝብ ድምጽ ክብር ያለመስጠት”፣ “ጸረ ዲሞክራሲያዊ” እና “አሳፋሪ” ሲል ፓርቲው አውግዞታል።

ቦዴፓ ከዚህም በተጨማሪ በቤኒሻንጉሉ ጉሙዝ ክልል መዋቅር ውስጥ ገብተው እየሰሩ ያሉ የፓርቲው አመራሮች “ህገ ወጥ የስራ ዝውውር እየተደረገባቸው ነው” የሚል ቅሬታ አለው። የፓርቲው የውጭ እና የአለም አቀፍ ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር መብራቱ አለሙ፤ የቦዴፓ ሊቀመንበር አቶ አመንቴ ገሺ በሁለት አመት ውስጥ ብቻ ሶስት የተለያዩ ተቋሞችን እንዲመሩ መደረጋቸውን በአብነት አንስተዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ካቢኔ እንዲቀላቀሉ የተደረገው፤ በሰኔ 2013 ዓ.ም. ከተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ በኋላ ነበር። በወቅቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባሉ በርካታ አካባቢዎች በጸጥታ ስጋት ምክንያት ምርጫ  ባለመደረጉ፤ በክልሉ አዲስ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል የምክር ቤት መቀመጫ ማሟላት አልተቻለም። 

ለቀሪ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ምርጫ እስኪደረግ ባለው ጊዜ በስልጣን ላይ የሚቆየውን ካቢኔ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በ2014 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል። በዚሁ መሰረት የቦዴፓ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አመንቴ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገጠር መሬት እና ኢንቨስትመንት ቢሮን እንዲመሩ በወቅቱ ተሹመዋል። 

ሆኖም አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አቶ አመንቴ ወደ ገጠር መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ እንዲዘዋወሩ ተደርገዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፈው ሰኔ የተደረገውን ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ ተከትሎ አዲስ መንግስት ሲመሰረት ደግሞ የቦዴፓው ሊቀመንበር የክልሉን የኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ እንዲመሩ ለሶስተኛ ጊዜ የካቢኔ አባልነት ሹመት አግኝተዋል። 

አቶ አመንቴ በኃላፊነት ከተሹሙባቸው መስሪያ ቤቶች በፍጥነት እንዲነሱ እና ወደ ሌላ ቢሮ እንዲዘዋወሩ የሚደረጉት፤  “በተመደቡበት ቦታ ጥሩ አፈጻጸም ማሳየት ሲጀምሩ” መሆኑን ዶ/ር መብራቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህ አይነቱ የስራ ዝውውር “ህገወጥ ነው” ሲሉ የቦዴፓ የውጭ እና የአለም አቀፍ ዘርፍ ኃላፊ ተችተዋል። 

በቦዴፓ ላይ ከሚደረጉት እነዚህን መሰል “ጫናዎች” በተጨማሪ የክልሉ መንግስት የፓርቲውን አመራሮች ጭምር እስከማሰር የዘለቀ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ዶ/ር መብራቱ ይገልጻሉ። የፓርቲው የሴቶች ክንፍ ዋና ጸሀፊ የሆኑት ወ/ሮ አበበች ደቻሳ፤ በቅርቡ ለአራት ቀናት ከታሰሩ በኋላ እንዲለቀቁ መደረጉንም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።  

ቦዴፓ በትላንቱ መግለጫው እስራትን ጨምሮ በአባላቱ፣ በደጋፊዎቹ እና አመራሮቹ ላይ እየደረሱ ያሉ ጫናዎችን  “የማያስተካክል” ከሆነ፤ ፓርቲው ከክልሉ መንግስት በጋራ ለመስራት ያሳለፈውን ውሳኔ እንደገና ለማጤን የሚገደድ መሆኑን አስታውቋል። የገዢው ፓርቲ አመራሮች “የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎችን መርጣችኋል” በሚል በህዝብ ላይ ያደረሱትን በደል፤ የፌደራል መንግስት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲያጣሩም ቦዴፓ ጠይቋል። 

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የአሶሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ጉርሜሳ በፉጣ ቦዴፓ በመግለጫው ያቀረበውን ቅሬታ መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፓርቲው በመግለጫው ላይ ያቀረበውን ቅሬታ ጽህፈት ቤቱ ማጣራት መጀመሩንም አስረድተዋል።

ቦዴፓ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በበኩሉ የፓርቲውን ቅሬታ በተመለከተ እስካሁን በይፋ የደረሰው አቤቱታ እንደሌለ ገልጿል። የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ደስታ ዲንቃ፤ በተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት እና አመራሮች ላይ “እስር” እና “ወከባ” በተለያየ ጊዜ እንደሚደርስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የቦዴፓም ቅሬታ ተጣርቶ፤ ችግሩ በጋራ ምክር ቤቱ ቤቱ በኩል እንዲፈታ ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)