የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስሩ ያለው የትግርኛ ቋንቋ እና ስነ ጹሁፍ ትምህርት ክፍል እንዲዘጋ ወሰነ

በናሆም አየለ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ18 ዓመት በፊት የተቋቋመውን የትግርኛ ቋንቋ እና ስነ ጹሁፍ ትምህርት ክፍልን፤ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ሊዘጋ ነው። በፍልስፍና ትምህርት ክፍል በመጀመሪያ ዲግሪ የሚሰጠው ትምህርትም፤ ከዚህ ዓመት ጀምሮ እንዲቋረጥ ዩኒቨርስቲው ውሳኔ አስተላልፏል።

አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ ከእዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው፤ የትምህርት ክፍሎቹ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት አዲስ ተማሪዎችን ባለመቀበላቸው ነው። የአልማዝ ኢዮቤሊዮውን ለማክበር የተቃረበው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ መሆኑን ተከትሎ በስሩ ያሉ የትምህርት ክፍሎችን በአዲስ መልክ በማደራጀት ላይ ይገኛል። 

ከመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ በመሆን የመጀመሪያው የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የመልሶ ማደራጀት ስራውን በማከናወን ላይ ያለው የተማሪዎች የትምህርት ክፍል ምርጫዎችን መሰረት በማድረግ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የመልሶ ማደራጀትን የሚመለከት የዩኒቨርሲቲው ሰነድ፤ “የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጎባቸው የሚቀጥሉ”፣ “የሚጣመሩ”፣ “ተዋህደው አዲስ የትምህርት ክፍል የሚመሰርቱ”፣ “የሚጠናከሩ” እና “የሚቋረጡ” የትምህርት አይነቶችን ዘርዝሯል። 

ዩኒቨርሲቲው እንዲቋረጡ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው የትምህርት አይነቶች መካከል የትግርኛ ቋንቋ እና ስነ ጹሁፍ ይገኝበታል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ሲሰጥ የቆየው፤ በትግርኛ ቋንቋ፣ ስነ ጹሁፍ እና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ስር ነበር። ሆኖም የትምህርት ክፍሉ ባለፉት ዓመታት ባጋጠመው የተማሪዎች እጥረት ምክንያት ከዘንድሮው የትምህርት ዘመን ጀምሮ እንዲዘጋ መወሰኑን የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ ሀድጉ ተካ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

“ትግርኛ ለምን ተማሪ እንዳጣ ዋናው ምክንያት የታወቀ ነው። በጦርነቱ ምክንያት ነው። እሱ ጎድቶናል። ተማሪው በየት አድርጎ ይምጣ” ሲሉ አቶ ሀድጉ የችግሩን ምክንያት አስረድተዋል። የትግርኛ ቋንቋ፣ ስነ ጹሁፍ እና ፎክሎር ትምህርት ክፍል አዲስ ተማሪዎችን ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበለው በ2010 ዓ.ም ነበር።

የትምህርት ክፍሉ፤ እነዚህን ተማሪዎች ለአራት አመታት አስተምሮ ካስመረቀ በኋላ ከመማር ማስተማር ሂደት ውጪ ሆኖ ቆይቷል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ክፍሉ እንዲዘጋ መወሰኑን ተከትሎ፤ በስሩ የነበሩትን አራት መምህራን ወደ ሌሎች ትምህርት ክፍሎች ማዛወሩን የትምህርት ክፍል ኃላፊው ገልጸዋል።

እርሳቸውን ጨምሮ ሶስት ባልደረቦቻቸው በምርጫቸው ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ እና ስነ ጹሁፍ ትምህርት ክፍል መዘዋወራቸውን እና አንደኛዋ መምህርት ደግሞ ወደ ጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መግባታቸውን አቶ ሀድጉ ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ዓመት ጀምሮ የትግርኛ ቋንቋ ትምህርትን መስጠት ቢያቋርጥም፤ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ እንግሊዘኛ፣ አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ እንዲሁም ቻይንኛ ቋንቋዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ ማስተማሩን እንደሚቀጥል በመልሶ ማደራጀት ሰነዱ ላይ አመልክቷል። 

እንደ ትግርኛ እና ቋንቋ ስነ ጽሁፍ ሁሉ በተመሳሳይ ምክንያት እንዲቋረጥ በዩኒቨርሲቲው ውሳኔ የተላለፈበት ሌላው የትምህርት አይነት፤ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የሚሰጠው የፍልስፍና ትምህርት ነው። የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ከ2011 ዓ.ም ወዲህ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀ ግብር አዲስ ተማሪዎችን አለመቀበሉን የትምህርት ክፍሉ ኃላፊው ዶ/ር ፋሲል መራዊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

እርሳቸው የሚመሩትን ጨምሮ በማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ክፍሎች የተማሪ እጥረት መታየት የጀመረው፤ “70/30” የተሰኘው የተማሪዎች ምደባ አሰራር ወደ ተግባር ከገባ በኋላ እንደነበር ዶ/ር ፋሲል ያስረዳሉ። ባለፉት አመታት ዩኒቨርሲቲውን የሚቀላቀሉ አዲስ ተማሪዎች፤ ፍልስፍና መማርን ምርጫቸው አለማድረጋቸው ሌላው እጥረቱን የፈጠረ ምክንያት እንደሆነ ያክላሉ። 

የፍልስፍና ትምህርት ክፍል በተማሪዎች እጥረት ምክንያት በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የሚሰጠውን ትምህርት እንዲያቋርጥ ቢገደድም፤ በማታው ክፍለ ጊዜ ግን ዘጠኝ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል። የትምህርት ክፍሉ እነዚህን የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የሚያስመርቀው በዚህ ዓመት ነው። 

ከእነዚህ ተማሪዎች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት 80 ተማሪዎች በማስተርስ እና በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ የፍልስፍና ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። የፍልስፍና ትምህርት ክፍል በሁለቱ መርሃ ግብሮች የሚማሩ ተማሪዎችን ዘንድሮም መቀበሉን እንደሚቀጥል ዶ/ር ፋሲል አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)