በሙሉጌታ በላይ
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው እና ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ የተሸጋገረው የኮሪደር ልማት፤ የከተማይቱን ነዋሪዎች “ሰብአዊ መብቶች የጣሰ ነው” ሲል የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ዛሬ በሰጠው መግለጫ ወቀሰ። በኮሪደር ልማቱ ሳቢያ“እያየለ የመጣው የህዝብ ብሶት እና ምሬት” በቸልታ ከታለፈ፤ “የህዝባዊ ቁጣ መገንፈል እና ተዛማጅ ጉዳዮችን” ሊያስከትል እንደሚችልም ፓርቲው አስጠንቅቋል።
አዲስ አበባ “ዓለም አቀፍ ደረጃዋን ጠብቃ የመልማቷ ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ” እንዳልሆነ በዛሬው መግለጫ የጠቀሰው ፓርቲው፤ ይሁን እንጂ የከተማዋ ልማት እና እድገት “ከኗሪው ህዝብ መብት መከበር” እና “ከጥቅሞቹ መጠበቅ” ተነጥሎ ሊታይ እንደማይገባ አሳስቧል። ልማቱ “ከዜጎች አጠቃላይ የኑሮ መስተጋብር እና የኢኮኖሚ እድገት ጋር የተጣጣመ” መሆን እንደሚኖርበትም ፓርቲው በአጽንኦት አንስቷል።
የዛሬውን መግለጫ የሰጡት የኢህአፓ የአዲስ አበባ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ አካሉ፤ በከተማይቱ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት “የበርካታ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች፣ አነስተኛ እና ከፍተኛ የንግድ ድርጅቶች” መፍረሳቸውን ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየወሰዳቸው ያላቸው እርምጃዎች “የነዋሪዎች ሁኔታ ያላገነዘቡ፣ ምቹ ጊዜን ያልጠበቁ እና ከግምት ያላስገቡ” መሆናቸውንም አመልክተዋል።
“በኮሪደር ልማት ምክንያት ነዋሪዎችን በማዋከብ፣ በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲፈርስ በመበየን፣ ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ የሚተላለፈው አጣዳፊ መመሪያ፤ የነዋሪዎችን መብት የሚደፈጥጥ፣ ጥቅማቸውን የሚጎዳ ትእዛዝ፤ ፍጹም አግባብነት የሌለው እና ሰብአዊ መብቶችን የጣሰ መሆኑን ፓርቲያችን ያምናል” ሲሉ አቶ አበበ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
እርሳቸው ይህን ቢሉም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግን፤ አስተዳደራቸው እያካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ግንባታ የሚከናወነው ከህዝብ ጋር “መተማመን” ላይ ከተደረሰ በኋላ መሆኑን ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ አስታወቀው ነበር። በኮሪደር ልማት ሳቢያ “የሚፈርሱ” እና “የሚነሱ” አካባቢዎች ካሉ፤“መጀመሪያ ከህዝብ ጋር” ውይይት እንደሚደረግ ከንቲባዋ በዚሁ መግለጫቸው አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ በሶስት ወር እንዲጠናቀቅ ቀነ ገደብ የተቀመጠለትን የመጀመሪያውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የጀመረው ባለፈው የካቲት ወር ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር የተከናወነለት ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት፤ 132 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 2,817 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ነው።
ሁለተኛው ምዕራፍ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በስምንት የከተማይቱ አካባቢዎች የሚተገበር እንደሆነ ባለፈው ሳምንት ይፋ ተደርጓል። የኢህአፓ የአዲስ አበባ ኮሚቴ ሰብሳቢ በዛሬው መግለጫቸው፤ የሁለተኛው ምዕራፍ አተገባበር ከመጀመሪያው የባሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
“የመጀመሪያ[ምዕራፍ]ላይ አይታችሁ ከሆነ፤ ፒያሳ አካባቢ በየአዳራሹ ሰዎችን ለማወያየት ተሞክሯል። የተሻለ ቤት ለመስጠት ተሞክሯል። መንግስት ከመጀመሪያው ምዕራፍ ይማራል የሚል እምነት ነበረን። ከዚያ በኋላ[የሆነውን] ነገር ስናየው ግን ቁልቁል እየወረደ ነው የመጣው”ሲሉ አቶ አበበ ተችተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ለነዋሪዎች ካለው ቸልተኝነት የተነሳ የህዝብን ድምጽ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማፍረስ፣ ማፈናቀል እና ማሳደዱን በመቀጠሉ፤ የህዝቡ ብሶት እና ምሬት እያየለ መጥቷል” ሲሉም አቶ አበበ ጉዳዩ የደረሰበትን ደረጃ አመልክተዋል። የከተማይቱ አስተዳደር፤ ለነዋሪዎች ምሬት “ትኩረት እና ቅድሚያ” በመስጠት አስፈላጊውን “የእርምት እርምጃ” በአፋጣኝ እንዲወስዱ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ነባራዊ ሁኔታ በቸልታ ማለፍ፤ “መላውን ህብረተሰብ ከባድ ዋጋ ሊያስከፍለው ወደሚችል የህዝባዊ ቁጣ መገንፈል እና ተዛማጅ ጉዳዮችን ሊያስከትል ይችላል”
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)
ይህ ሳይሆን ቀርቶ “ሁኔታዎች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ”፤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከፍተኛ ምሬት “ወደ ቁጣ ሊለወጥ ይችላል” የሚል ስጋት እንዳለው ኢህአፓ በመግለጫው ጠቁሟል። የከተማይቱን ነዋሪዎች ነባራዊ ሁኔታ በቸልታ ማለፍ፤ መላውን ህብረተሰብ “ከባድ ዋጋ ሊያስከፍለው ወደሚችል የህዝባዊ ቁጣ መገንፈል እና ተዛማጅ ጉዳዮችን ሊያስከትል ይችላል” ሲል ፓርቲው አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)