የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው መጠለያዎች “የታጠቁ አካላት ሰርገው በመግባት” ጥቃት እንደሚፈጽሙ ኢሰመኮ አስታወቀ

በሙሉጌታ በላይ

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚኖሩባቸው ጣቢያዎች “ተገቢ ጥበቃ ስለማይደረግላቸው”፤ የታጠቁ አካላት “ሰርገው በመግባት ጥቃት እንደሚፈጽሙ” የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በዚህ ሳቢያ ተፈናቃዮች “አስጊ በሆነ የደህንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ” ኮሚሽኑ ገልጿል።

ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ይህን ያስታወቀው፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 18፤ 2017 ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ነው። ኮሚሽኑ ለሶስተኛ ጊዜ ያዘጋጀው ዓመታዊ ሪፖርት፤ ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ  2016 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው። 

በስምንት ክልሎች የተፈናቃዮቹን ሰብአዊ መብቶች አያያዝን የተመለከተ ክትትል እና ምርመራ ማድረጉን በሪፖርቱ የገለጸው ኢሰመኮ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የታጠቁ ቡድኖች በየጊዜው በሚያደርሱት ማንነትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ዜጎች እንደሚፈናቀሉ አመልክቷል። በመንግስት እና በታጠቁ ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

በተፈጥሯዊ አደጋዎች እንዲሁም በልማት ፕሮጀክቶች ሳቢያ ዜጎች ከሚኖሩበት ቀዬ እንደሚፈናቀሉም በኢሰመኮ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል። በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያለው የጸጥታ ችግር፤ ዜጎችን እንዲፈናቀሉ ከማድረግ ባሻገር ለተፈናቃዮች ሊደረግ የሚገባውን ሰብአዊ ድጋፍ እና ጥበቃ “አስቸጋሪ” እንዳደረገው በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ ተገልጿል። 

በሶስቱ ክልሎች ባለው የጸጥታ ችግር  ምክንያት ተፈናቃዮች “ድጋፍ እና ጥበቃ” እንደማያገኙ ያመለከተው ኮሚሽኑ፤ በዚህም ምክንያት በታጣቂዎች የተገደሉ ዜጎች መኖራቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። ከኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ቦራ ወረዳ ተፈናቅለው በመቂ ከተማ ከሚኖሩ ተፈናቃዮች ውስጥ አራቱ ባለፈው ዓመት ህዳር ወር “በኦነግ ሸኔ” መገደላቸውን ኢሰመኮ ለዚህ በማሳያነት ጠቅሷል።

በዚህ ጥቃት ሳቢያ ተፈናቃዮች “በነጻነት በፈለግነው ሰዓት ለመንቀሳቀስ ስጋት ፈጥሮብናል” ማለታቸውን የኮሚሽኑ ሪፖርት አመልክቷል። ጥቃቱን የፈጸሙ ሰዎች “ተይዘው ለህግ ባመቅረባቸው”፤ ከተለያዩ አካላት “ዛቻ እና ማስፈራሪያ” እየደረሰባቸው መሆኑን እንደገለጹለትም ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ አስታውቋል።

እንደ ኦሮሚያ ክልል ሁሉ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ በማንቡክ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችም፤ ተገቢው ጥበቃ የማይደረግላቸው መሆኑን ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ አስቀምጧል። በዚህ መጠለያ ጣቢያ ግድያ እና የሴቶች ጠለፋ መፈጸሙንም ኮሚሽኑ ገልጿል። 

በአማራ ክልል፣ ሰሜን ወሎ ዞን፣ ጃራ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተመሳሳይ ስጋት ያለባቸው መሆኑም በኢሰመኮ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል። ተፈናቃዮቹ፤ የአማራ ክልልን “አልፈው የሚመጡ ታጣቂዎች” አድርሰውታል ባሉት “ተደጋጋሚ ጥቃት” “የደህንነት ስጋት” እንዳለባቸው መናገራቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አትቷል።

“የታጠቁ አካላት” በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት፤ መጠለያዎች እና ማቆያ ጣቢያዎች “ተገቢው ጥበቃ” ስለማይደረግላቸው መሆኑን ኢሰመኮ አስገንዝቧል። ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው ቦታዎች “የሲቪል እና የሰብአዊነት ባህሪ” ሊከበር ይገባው እንደነበር ኮሚሽኑ አመልክቷል።

መንግስት ወደ እነዚህ ቦታዎች የታጠቁ ቡድኖች ወይም አካላት ሰርገው በመግባት ጥቃት እንዳይፈጽሙ “ተገቢውን ጥበቃ እና ክትትል እንዲያደርግም” ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም አሳስቧል። የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፤ መፈናቀልን ባስከተሉ አሊያም ድርጊቱ እንዳይፈጸም የመከላከል እና ምላሽ የመስጠት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ አካላት “ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ” ጥሪ አቅርበዋል።

ኢሰመኮ ዓለም አቀፉን የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) መረጃ ጠቅሶ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር 3.3 ሚሊዮን መድረሱን በዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ አስፍሯል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) ከአምስት ወራት በፊት ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ 4.5 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዳሉ አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)