“አንዳንድ ሀገራት ኢትዮጵያን መዝረፍ መብት እንደሆነ የሚያስቡ አሉ”- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 

ኢትዮጵያን “መዝረፍ”፤ “መብት እንደሆነ” የሚያስቡ “አንዳንድ ሀገራት አሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሱ። የኢትዮጵያን ሀብት “የመዝረፍ” እና “የውጭ ምንዛሬ ቢዝነስ የሚሰሩ” ኤምባሲዎች አሉ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንጅለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 21፤ 2017 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው፤ ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። በሁለት ክፍል በተከፈለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ቅድሚያውን ያገኙት፤ ከኢኮኖሚ ጉዳዮች ጋር በተያያዙ ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾች ናቸው። 

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዘርፍ፤ በገቢ፣ በሬሚታንስ፣ በውጭ ኢንቨስትመንት፣ በወርቅ እና በቡና የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) “እድገት ማስመዘገቡን” በቁጥር በማስደገፍ ገለጻ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች” ያሏቸውን ጉዳዮችንም ለፓርላማ አባላት ዘርዝረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አብይ በተለይ በአጽንኦት ያነሱት፤ በባንኮች፣ በኤምባሲዎች እና በኩባንያዎች ይፈጸማሉ ያሉትን “የጥቁር ገበያ” ንግድ ነው። 

በሀገሪቱ ያሉ ባንኮች በህጋዊ መንገድ ከሚሰራው ይልቅ፤ “በትይዩ” የውጭ ምንዛሬ ገበያ በመሳተፍ “ኮሚሽን ማግኘት” እንደለመዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። “ባንክ በህጋዊ መንገድ የሚወዳደሩበት እንጂ በህገ ወጥ መንገድ በኮሚሽን ሀብት የሚሰበስቡበት መሆን የለበትም” ሲሉም ተደምጠዋል።  

“ባንኮች ህግ እና ስርአት አክብረው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚክ እድገት በሚያረጋግጥ መንገድ ሊሰሩ ይገባል እንጂ፤ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና ተቃሚዎች፤ ባንክ በሚል ስም የአራጣ ስራ የሚሰሩ ከሆነ ችግር ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ተግባር ላይ በሚሳተፉ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ ይወስዳል ብለዋል። 

“የኢትዮጵያ የፋይናንሺያል ስርዓት ጤናማ በሆነ መንገድ እንዳያድግ የሚያበላሹ ግለሰቦች እና ቡድኖች አሉ። የሚዘርፉ ማለት ነው። እነርሱ ላይ ከፍተኛ ክትትል እና እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል። ሆኖም አብይ ይህን ተግባር ይፈጽማሉ ያሏቸውን ባንኮች፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች ማንነት ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።


እንደ ባንኮች ሁሉ “በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ ንግድ ይሳተፋሉ” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወነጀሉት “አንዳንድ” የውጭ ሀገር ኤምባሲዎች ናቸው። ኤምባሲዎቹ ከዚህ ንግድ ተሳትፏቸው በተጨማሪም “የኢትዮጵያን ሀብት ይዘርፋሉ” ሲሉ አብይ፤ “የማይታረሙ ከሆነ” በእነርሱ ላይም “ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

“ጤናማ ዝምድና የማያደርግ ማንም ኤምባሲ፤ እኛ አንፈልግም። እኛ የምንፈልገው ጤናማ፣ ህጋዊ ስርዓት ያለው መንገድ የሚከተል ብቻ ነው። ያን ስራ የሚሰሩ፣ ነገር እንዳናበላሽ የታገስናቸው፣ ስራቸው ግን የblack market ማሯሯጥ የሆኑ ኤምባሲዎች አሉ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አንዳንድ ኤምባሲዎች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ሀገራትም፤ “ኢትዮጵያን መዝረፍ መብት እንደሆነ የሚያስቡ አሉ” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል። ኢትዮጵያ ይህን በተመለከተ “ከብሔራዊ ጥቅሟ አንጻር” ጥያቄ ስታነሳ፤ እነዚህ ሀገራት “ግሰላ ይሆናሉ” ሲሉም ተናግረዋል።

“ጤናማ ዝምድና የማያደርግ ማንም ኤምባሲ፤ እኛ አንፈልግም። እኛ የምንፈልገው ጤናማ፣ ህጋዊ ስርዓት ያለው መንገድ የሚከተል ብቻ ነው”

– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

“እኛን መዝረፍ እና የእኛን ብሔራዊ ጥቅም አለማክበር ተገቢ አይደለም። ከእኛ መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ለመስጠት ደግሞ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። 

አብይ በዘረፋ ላይ ተሰማርተዋል ያሏቸውን ሀገራት ባይጠቅሱም፤ ዶላር እና ወርቅ ከኢትዮጵያ ወደ አንዳንድ ሀገራት “በባቡር እና በቅጥቅጥ መኪና” ጭምር ተጓጉዞ እንደሚወጣ አስገንዘበዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የፓርላማ አባላቱ ትኩረት እንዲያደርጉ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በውስጣችን ያሉ ሰዎች ተጨምረውበት የሚደረግ ማንኛውም ህግ ያልተከተለ ዘረፋ መከላከል አለብን” ሲሉ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]