ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የምታበድረውን ገንዘብ፤ በድፍድፍ ነዳጅ ለማስከፈል የሚያስችል አማራጭ የያዘ ስምምነት በፓርላማ ጸደቀ 

በቤርሳቤህ ገብረ

ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ለምትበደረው 738.26 ሚሊዮን ዶላር፤ ወደፊት የምትፈጽመውን ክፍያ በድፍድፍ ነዳጅ እንድትመልስ አማራጭ የሚሰጥ የብድር ስምምነት በፓርላማ ጸደቀ። በብድር ስምምነቱ የሚገኘው ገንዘብ፤ በደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ከምትገኘው ፓጋክ ከተማ በመነሳት እስከ ፓሎች ከተማ ድረስ ያለውን 220 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት የሚያስችል ነው።

በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል የተደረገው የብድር ስምምነት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 26፤ 2017 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በቀረበበት ወቅት፤ ማብራሪያውን በንባብ ያሰሙት በፓርላማ የመንግስት ዋና ተጠሪው ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው። ዶ/ር ተስፋዬ የብድር ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለተግባራዊነቱም የተለያዩ የዝግጅት እና የትብብር ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል። 

በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ በመገኘት ተጨማሪ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ፤ የብድር ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የሚያስገኛቸውን ፋይዳዎች ዘርዝረዋል። ስምምነቱ ቀጠናዊ ትስስርን እና የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትስስርን ከማጠናከር ባሻገር በጸጥታ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያመጣ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ብድር የምትሰጥበት የስምምነት ሰነድ በዛሬው ዕለት ለፓርላማ ይቀርብ እንጂ፤ ሁለቱ ሀገራት ስምምነቱን የተፈራረሙት በግንቦት 2015 ዓ.ም ነበር። የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዳት በተገኙበት በጁባ ከተማ በተካሄደው የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ፤ ኢትዮጵያን በመወከል ፊርማቸውን ያኖሩት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር እዮብ ነበሩ። 

ደቡብ ሱዳን በብድር የምታገኘው ገንዘብ፤ በጋምቤላ በኩል ካለው የኢትዮጵያ ድንበር በመነሳት በነዳጅ ሀብት ወደ በለጸገው ፓሎች አካባቢ የሚዘረጋውን መንገድ ወደ አስፋልት ለማሳደግ የሚውል ነው። የመንገድ ፕሮጀክቱ የሲቪል እና የአማካሪ ስራዎች የሚከናወኑት በኢትዮጵያውያን ኮንትራክተሮች እንደሆነ በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል። 

በኢትዮጵያ በኩል የመንገድ ፕሮጀክቱ የሚመራው በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ነው። የደቡብ ሱዳን መንገዶች ባለስልጣን በደቡብ ሱዳን በኩል ተመሳሳይ ኃላፊነት እንደሚወስድ በስምምነቱ ላይ ሰፍሯል። ለፕሮጀከቱ ማስፈጸሚያ ይውል ዘንድ ከኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠው የ738.26 ሚሊዮን ዶላር ብድር፤ በውጪ ምንዛሬ ከሚፈለጉት የውጪ ስራዎች በስተቀር በብር የሚከፈል እንደሆነ ዶ/ር ተስፋዬ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ላይ አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በስምምነቱ መሰረት የደቡብ ሱዳን መንግስት አምስት አመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ፤ በ10 ዓመታት የጊዜ ገደብ ውስጥ አጠቃላይ ብድሩን ከፍሎ መጨረስ ይጠበቅበታል። የብድር ክፍያው እኩል በሆነ መጠን ተከፋፍሎ፤ በየሶስት ወሩ መከፈል እንዳለበት በስምምነቱ ላይ ተመላክቷል። 

ደቡብ ሱዳን፤ የብድር ክፍያውን በጥሬው አሊያም ብድሩን ያለውን ዋጋ የሚስተካከል ድፍድፍ ነዳጅ እስከ ፖርት ሱዳን ድረስ ማቅረብ እንደለባትም በስምምነቱ ላይ ሰፍሯል። የድፍድፍ ነዳጁ ዋጋ የሚወሰነው፤ በክፍያው ወቅት በአረብ ባህረ ሰላጤ ሀገራት የሚኖረውን ዋጋ በማመሳከሪያነት በመውሰድ መሆኑን በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪው ዶ/ር ተስፋዬ ለፓርላማ አባላት አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያደረገችውን የብድር ስምምነት አስመልክቶ አስተያየት የሰጡ የፓርላማ አባላት፤ ስምምነቱን በአዎንታዊነት ተመልክተውታል። ስምምነቱን ለማጽደቅ ድምጽ በተሰጠበት ወቅትም፤ ከአንድ ድምጸ ተአቅቦ በስተቀር ሁሉም አባላት ድጋፋቸውን ቸረውታል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አቶ ዘካሪያስ ኤርኮላ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ቀጠና “ትልቅ የትስስር መሰረት” እንደሚሆን ገልጸዋል። እኚሁ የፓርላማ አባሉ፤ ፕሮጀክቱን በበላይ እንደሚመራ በስምምነቱ ላይ የተገለጸው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መስሪያ ቤት “ትልቅ ኃላፊነት” እንዳለበት አሳስበዋል። የመንገድ ግንባታው፤ በሀገር ውስጥ እንደሚዘገዩ እና እንደሚስተጓጎሉ ፕሮጀክቶች ሳይሆን፤ መንግስት የጸጥታ መዋቅር ድጋፍ አድርጎ በተፋጠነ ሁኔታ መካሄድ እንደሚገባውም የፓርላማ አባሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለዚህ አስተያየት ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር እዮብ፤  የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም “ከፍተኛ ዝግጅት” ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል። ተቋሙ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት፤ የተወካዮች ምክር ቤት የስምምነት ሰነዱን እስኪያጸድቅ እየተጠባበቀ መሆኑንም አክለዋል። 

“በአጠቃላይ የዚህን ፕሮጀክት ፋይዳ በመገንዘብ፤ ተቋሙ ባለፉት ወራት ሲያጠና፣ ሲዘጋጅ ነው የቆየው። ይህ ስምምነት እንደጸደቀ በፍጥነት ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት ያደርጋል” ሲሉም ዶ/ር እዮብ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፤ ለመንገድ ፕሮጀክቱ “አቅም ያላቸውን ኩባንያዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ በመምረጥ ስራው እንዲሰራ እንደሚያደርግም” ሚኒስትር ዴኤታው ማስተማመኛ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)