ከኦሮሚያ ክልል ለሀገራዊ ምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሂደት ከነገ ጀምሮ ሊካሄድ ነው

በናሆም አየለ

ከኦሮሚያ ክልል በሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሂደት ከነገ ሰኞ ታህሳስ 7፤ 2017 ጀምሮ ለተከታታይ ስምንት ቀናት ሊካሄድ ነው። በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ላይ ስምንት ሺህ የሚጠጉ የማህበረሰብ ክፍል ወኪሎች እና የክልል ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታውቋል። 

በአዳማ ከተማ የሚካሄደው ይህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፤ በሀገራዊ ምክክር የተዘጋጁ ተመሳሳይ መድረኮችን ቁጥር 12 ያደርሰዋል። የኦሮሚያ ክልል በወረዳ እና በዞን ብዛቱ “ከፍተኛ ቁጥር” ያለው መሆኑ፤ የአሁኑን የምክክር መድረክ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት የተለየ እንደሚያደርገው ተገልጿል። 

በአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኩ ላይ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ 356 ወረዳዎች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ዛሬ እሁድ በአዳማ ከተማ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ተሳታፊዎቹ የወከሏቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፤ የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተፈናቃዮች፣ የተገለሉ ማህበረሰቦች እና የህብረተሰብ መሪዎች ናቸው። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከኦሮሚያ ክልል ተሳታፊዎችን የመረጠው ክልሉን በአራት ክላስተሮች በመከፋፈል ነው። በጅማ፣ ሻሸመኔ፣ አዳማ እና ሀረርጌ ከተፋፈሉት በእነዚህ ክላስተሮች ከሚገኙ ወረዳዎች የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች የተመረጡት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ነበር። ሆኖም በወቅቱ “የባሰ የጸጥታ ስጋት” አለባቸው በተባሉ ስድስት ወረዳዎች ውስጥ የተወካዮች ምርጫ አልተካሄደም። 

“በጸጥታ ስጋት” ምክንያት ተወካዮቻቸውን ያልመረጡት ነጆ፣ ባቦገቤል፣ ምዕራብ ወላቡ፣ ጉሚ ኤልዴሎ፣ ደራ እና ቶሌ ወረዳዎች ናቸው። በአሁኑ ወቅት በእነዚህ አካባቢዎች “ሁኔታዎች እየተረጋጉ በመምጣታቸው”፤ በአዳማ ከተማ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች ከወረዳዎቹ ማስመረጥ መቻሉን ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በነገው ዕለት በሚጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከስድስቱ ወረዳዎች የተመረጡትን 72 ተሳታፊዎች ጨምሮ ቁጥራቸው ሰባት ሺህ የሚጠጋ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች እንደሚሳተፉ ዶ/ር ዮናስ ገልጸዋል። እነዚህ ተወካዮች፤ በሀገር አቀፍ ጉባኤ በሚቀርቡ የአጀንዳ ሃሳቦች ላይ ለአምስት ቀናት ምክክር እንደሚያደርጉም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮቹ፤ በኦሮሚያ ክልል ካሉ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የክልሉን አጀንዳዎች የመለየት ሂደት በቀሪዎቹ ሶስት ቀናት ያከናወናሉ። የክልል ባለድርሻ አካላት የሚባሉት፤ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አካላት፣ ማህበራት እና ተቋማት፣ ታዋቂ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች ናቸው።

ከባለድርሻ አካላት እና ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል የተመረጡ ተወካዮች፤ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ “ሊመከርባቸው ይገባሉ” የተባሉ የኦሮሚያ ክልል አጀንዳዎችን በመለየት በሂደቱ ማጠቃለያ ላይ ለኮሚሽኑ እንደሚያስረክቡ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በተመሳሳይ መልኩ አጀንዳዎችን  ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ተረክቧል። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከዘጠኙ ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳድሮች አጀንዳዎችን ሰብስቦ ቢጨርስም፤ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ግን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣን እንኳ ገና አላከናወነም። ኮሚሽኑ ከሁለቱ ክልሎች አጀንዳዎችን ሳይሰበስብ ሀገር አቀፍ ጉባኤ ለማድረግ አቅዶ እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ዮናስ፤ ኮሚሽኑ ይህን በተመለከተ ሁለት አካሄዶችን ለመከተል ማሰቡን ተናግረዋል። 

“ሀገራዊ ጉባኤ ለማከናወን በእኛ በኩል እቅዱ አለ። በዚያ ውስጥም ሁሉም እንዲገኙ የእኛ ፍላጎት ነው። የቀሩት አማራ እና ትግራይ ተጠቃለው እንዲገቡ እንፈልጋለን። የአሰራር መንገዳችንን ቀየር አድርገን፤ እንደ ሌላው አካባቢ በሶስት ወር በአራት ወር ሳይሆን ለየት አድርገን አጣድፈን፤ ካሉት የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ አመራሮች፣ ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር አድርገን፤ መጨረሻ ላይ አንድ ላይ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን” ሲሉ ኮሚሽነር ዮናስ  ተቋሙ ሊተገብር ያቀደውን አንደኛውን አካሄድ አብራርተዋል። 

ኮሚሽኑ ባቀደው ጊዜ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤን ማካሄድ የማይችል ከሆነ፤ “የስራ ዘመኑ እንዲራዘም የሚጠየቅ” መሆኑን  ዶ/ር ዮናስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። የኮሚሽነሩ ምላሽ፤ ባለፈው ወር በፓርላማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ከተንጸባረቀው የኮሚሽኑ አቋም የሚቃረን ነው። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ህዳር 10፣ 2017 ለፓርላማ ባቀረበበት ወቅት፤ ኮሚሽኑ የስራ ዘመኑ እንዲጨመርለት ጥያቄ እንደማያቀርብ በስብሰባው የተገኙት ፕሮፌሰር መስፍን እና ሌሎች ሁለት ኮሚሽነሮች አስታውቀው ነበር። “ጊዜን በተመለከተ እኛ ይሄን ያህል ጊዜ ይሰጠን ወይም እንዲህ ይደረግልን ለሚለው ጥያቄ አይደለም ዝግጅታችን። እኛ ዝግጁነታችን በቀረን ጊዜ ውስጥ intensively ሰርተን የት መድረስ እንችላለን [ነው]” ሲሉ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር በወቅቱ መናገራቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)