ኢትዮ ቴሌኮም በድምጽ እና ጥቅል አገልግሎቶቹ ላይ የታሪፍ ቅናሽ አደረገ

በሃሚድ አወል

ኢትዮ ቴሌኮም ከነገ ጀምሮ በአጠቃላይ ጥቅል አገልግሎት ላይ የ20 በመቶ ቅናሽ ማድረጉን አስታወቀ። ጥቅል ሳይገዙ የድምጽ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ደንበኞችም ከ20 እስከ 30 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ ማድረጉን ገልጿል። 

በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ማሻሻያዎች ማድረጉን የገለጸው የ2014 የበጀት ዓመት ዕቅዱን አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ በአዲስ አበባው ሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም ከጥቅል አገልግሎት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ማሻሻያዎች ማድረጉን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በመግለጫው ላይ አስታውቀዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ ብቸኛው የቴሌኮም አግልግሎት ሰጪው ተቋም ከጥቅል አገልግሎት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ማሻሻያዎች ማድረጉን አስታውቀዋል
ፎቶ፦ ኢትዮ ቴሌኮም

ተቋሙ ከነገ አርብ ነሐሴ 14፤ 2013 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ካለው የ20 በመቶ የጥቅል አገልግሎት ቅናሽ ባሻገር፤ ደንበኞች የገዙትን ጥቅል ማጋራት የሚችሉበትን አሰራር እንደሚጀምር ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል። ደንበኞች የገዙትን ጥቅል አገልግሎት፤ ከድምጽ ወደ ኢንተርኔት ወይም ከመልዕክት ወደ ድምጽ፣ ወደ ፈለጉት ጥቅል መቀየር የሚችሉበት አማራጭንም ተቋሙ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምርም ጠቁመዋል። 

እነዚህ አገልግሎቶች ተግባራዊ መሆን የሚጀምሩበትን ቀን ተቋሙ ወደ ፊት እንደሚያሳውቅም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል። ደንበኞች የራሳቸውን ጥቅል መቅረጽ የሚችሉበት አሰራርን ግን ከነሐሴ 26 ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምር አብራርተዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም 175 የጥቅል አገልግሎት አይነቶች የነበሩት ሲሆን ከእነርሱ ውስጥ “ደንበኞች በብዛት አይጠቀሙባቸውም” የተባሉ የጥቅል አገልግሎቶች እንዲቋረጡ መደረጋቸው በዛሬው መግለጫ ላይ ተመልክቷል። ተቋሙ ከጥቅል አገልግሎት ማሻሻያዎች በተጨማሪ ከሶስት ደቂቃ በላይ የድምጽ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ደንበኞችም የታሪፍ ቅናሽ ማድረጉንም ዛሬ ይፋ አደርጓል። 

ኢትዮ ቴሌኮም በ2014 የበጀት ዓመት 70 ቢሊዮን ብር ለማግኘት አቅዷል

ከሶስት እስከ አስር ደቂቃ የድምጽ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ደንበኞች ከመደበኛው ታሪፍ የ20 በመቶ ቅናሽ መደረጉን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ በዛሬው መግለጫ ተናግረዋል። ከአስር ደቂቃ በላይ ለሚጠቀሙ ደንበኞች ደግሞ የ30 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ መደረጉንም አክለዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም በ2014 የበጀት ዓመት 70 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ያቀደ ሲሆን ይህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ካገኘው ካገኘው የ24 በመቶ ጭማሪ ይኖረዋል ተብሎ ተገምቷል። ተቋሙ ባለፈው ዓመት ያገኘውን 166.5 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬን በሰባት በመቶ የማሳደግ እቅድ ይዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)