ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 93.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

በሙሉጌታ በላይ

ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት፤ 93.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ ከተገኘው አጠቃላይ ገቢ 21.79  ቢሊዮን ብር የሚሆነው የተጣራ ትርፍ ነው ተብሏል።

ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ያስታወቀው የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸምን በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 3፤ 2016 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ የሚመሩት ተቋም ዘንድሮ ያገኘው ገቢ “ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 21.7 በመቶ ወይም 16.7 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ያገኘበት ነው ” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅራቢ ተቋም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያገኘው ገቢ፤ የእቅዱን 103.6 በመቶ ያሳካበት እንደሆነ ገልጸዋል። ኢትዮ ቴሌኮም በባለፈው የ2015 በጀት ዓመት ያገኘው ገቢ 75.8 ቢሊዮን ብር ነበር። ተቋሙ በዚህ ወቅት ካገኘው ገቢ ውስጥ 18.78 ቢሊዮን ብር የሚሆነው የተጣራ ትርፍ መሆኑም አስታውቆ ነበር።

ኢትዮ ቴሌኮም በዘንድሮው በጀት ዓመት ያገኘው 21.79 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ “በውጭ ኦዲተሮች ኦዲት ያልተደረገ” መሆኑን ፍሬሕይወት  አስገንዝበዋል። የትርፍ ገቢው “ኦዲት ተደርጎ” ወደፊት በተቋማቸው እንደሚገለጽም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙለት ምርት እና አገልግሎቶቹ፤ 198 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘቱንም ፍሬሕይወት በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል። ይሄ የእቅዱን 117.5 በመቶ ያሳካ መሆኑንም አመልክተዋል። “የዛሬ ዓመት 164 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነበር የተገኘው። ከዚህ አንጻር ካያችሁት ወደ 33.9 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ጭማሪ አለው” ሲሉ አክለዋል ።

በ2016 በጀት ዓመት የደንበኞቹን ብዛት 78 ሚሊዮን ለማድረስ እቅድ ይዞ የነበረው ኢትዮ ቴሌኮም፤ የእቅዱን 100.4 በመቶ በማሳካት 78.3 ሚሊዮን ደንበኞች ማፍራቱም በዛሬው መግለጫ ተጠቅሷል። ከእነዚህ የተቋሙ ደንበኞች ውስጥ 75.5 ሚሊዮን የሚሆኑት የሞባይል ድምጽ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ 40.4 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መሆናቸው ተነግሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)