“የፌደራል መንግስት አግባብነት ያላቸው እርምጃዎችን መወሰድ አለበት ስንል፤ ጦር አዝምቶ፣ ጦርነት ይቀስቅስ እያልን አይደለም” – አቶ ጌታቸው ረዳ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ የፌደራል መንግስት “አግባብነት ያላቸው እርምጃዎችን” እንዲወስድ ያሳሰበው፤ “ጦር እንዲያዘምት” እና “ጦርነት እንዲቀስቀስ አይደለም” ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። የጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባ ያቀረበው “ፎርማል ጥያቄ” እንደሌለም ፕሬዝዳንቱ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው ይህን ያሉት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 4፤ 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባው ሸራተን አዲስ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። በአዲስ አበባ ካሉ ጋዜጠኞች ጋር በዚህ አይነት መልኩ ሲገናኙ ከስምንት በኋላ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የገለጹት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት፤ ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። 

በጋዜጣዊ መግለጫ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች አንዱ፤ የፌደራል መንግስት “በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባ በይፋ ያስገባችሁት ጥያቄ አለ ወይ?” የሚል ነበር። አቶ ጌታቸው ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “በምክር ቤት ደረጃ፣ በካቢኔ ደረጃ ተሰብስበን የቀረበ ጥያቄ የለም። ጥያቄም ያስፈልገዋል የሚል እምነት የለኝም” ብለዋል። 

እርሳቸው የሚመሩት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ በትግራይ ክልል ላለው ወቅታዊ ሁኔታ የፌደራል መንግስት “አስፈላጊውን ድጋፍ” እንዲያደርግ አሳስቦ ነበር።“ጦርነትን ለማስወገድ የሚያስችሉ ‘ሁሉም አስፈላጊ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው’ የሚል እምነት አለን” ሲሉ በዛሬው መግለጫቸው የተደመጡት አቶ ጌታቸው፤ ወደ አዲስ አበባ የመጡት በዚሁ ጉዳይ ላይ ከፌደራል መንግስት ጋር ለመወያየት መሆኑን ጠቁመዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በትላንትናው መግለጫው ያነሳው “የፕሪቶሪያ ውል” ጉዳይንም፤ አቶ ጌታቸው ከፌደራል መንግስት ጋር አያይዘው በዛሬው መግለጫቸው ላይ አንስተዋል። የትላንቱ የጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ፤ “የፕሪቶሪያ ውል ሲፈርስ እና የትግራይ ህዝብ ወደ ዳግም ጥፋት ሲገባ ዝም ተብሎ መታየት የለበትም” ሲል የፌደራል መንግስት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት አሳስቦ ነበር። 

አቶ ጌታቸው በዛሬ መግለጫቸው በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር “አደጋ ላይ መውደቁን” አስረድተዋል። “የፌደራል መንግስት በራሱ ተሳትፎ፣ በራሱ ፍቃድ የተቋቋመ መንግስት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ፤ አደጋውን የመቀልበስ ግዴታ ይኖርበታል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሚመሩት መንግስት የሚጠበቀውን ጠቁመዋል።

የፌደራል መንግስት እንዲወስዳቸው የሚፈልጓቸው እርምጃዎች፤ “ጦርነት የሚያንዣብብትን ሂደት ለማስቀረት የሚያስችል” እንጂ ትግራይን ወደ ሌላ ዙር ጦርነት የሚያስገባ መሆን እንደሌለበት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አመልክተዋል። የፌደራል መንግስት “አግባብነት ያላቸው እርምጃዎችን መወሰድ አለበት ስንል ጦር አዝምቶ፣ ጦርነት ይቀስቅስ እያልን አይደለም” ሲሉም አቶ ጌታቸው አብራርተዋል። 

“እኔ እንደ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋናው ራስ ምታቴ፣ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ትግራይ ውስጥ ሌላ ጦርነት ተከፍቶ ህዝባችን ወደ መከራ የሚገባበት ሁኔታ ማስቀረት እንጂ፤ ‘ኑ እንግጠም’ ብለህ መሟገት አይደለም። ግን ‘እንግጠም’ ብሎ የሚፎከርን ኃይል አደብ ለማስገዛት ፌደራል መንግስቱ መግለጫ መስጠትም፣ ሌሎች ከዚያ በላይ መሄድ ያለባቸውን እንቅስቃሴዎች ካሉ፤ የእኔ ግብዣ ያስፈልገዋል የሚል እምነት የለኝም” ሲሉ አቶ ጌታቸው ይፋዊ ጥያቄ ለፌደራል መንግስት ያላቀረቡበትን ምክንያት አስረድተዋል። 

“እኔ እንደ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋናው ራስ ምታቴ፣ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ትግራይ ውስጥ ሌላ ጦርነት ተከፍቶ ህዝባችን ወደ መከራ የሚገባበት ሁኔታ ማስቀረት እንጂ፤ ‘ኑ እንግጠም’ ብለህ መሟገት አይደለም”

– አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት

የፌደራል መንግስት “የኢትዮ-ኤርትራን ድንበርን ለመጠበቅም” ሆነ በትግራይ ያሉ “የመከላከያ ካምፖችን ለመረከብ”፤ የእርሳቸውን “ፍቃድ” አሊያም “ጥሪ” እንደማያስፈልገው አቶ ጌታቸው ጨምረው ገልጸዋል። “ትግራይ ውስጥ የሚፈጠር ጦርነት ሌሎች ጠላቶችን ይጋብዛል ብቻ ሳይሆን ራሱን ችሎ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በቂ አቅም [አለው]” ያሉት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት፤ የፌደራል መንግስቱ ይህን የማስቆም “ኃላፊነት” እንዳለበት አስገንዝበዋል።  

“የኢትዮጵያን ሰላም ለማስጠበቅ ፈቃደኛ የሆነ መንግስት፤ በምንም መልኩ እንደዚህ አይነቱ ቀውስ አሁን ባለበት እንዲቀጥል ወይም ከዚህ በባሰ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል መፍቀድ ስለሌበት”፤ የፌደራል መንግስት “የራሱን ኃላፊነት” መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)