በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምሥረታ ላይ ያሉ “የኮንቶማ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” እና “የደንጣ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዳያካሂዱ በጸጥታ ኃይሎች መከልከላቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በዜጎች የመደራጀት እና የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት ዴሞክራሲያዊ መብት ላይ “የማስተጓጎል ተግባራት” የሚፈጽሙ አካላት ላይ የክልሉ የመንግሥት “ተገቢውን የእርምት እርምጃ” እንዲወስዱ ቦርዱ “በጥብቅ” አሳስቧል።
ምርጫ ቦርድ ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 15፤ 2018 ባወጣው መግለጫ፤ የሁለቱም ፓርቲዎች ተወካዮች ፓርቲ ለመመሥረት የሚያስፈልጉ ሁሉንም ሕጋዊ ሠነዶች አሟልተው ጠቅላላ ጉባዔያቸውን እንደሚያካሄዱ ለቦርዱ አሳውቀው እንደነበር ጠቅሷል። በዚህም መሰረት የኮንቶማ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጥቅምት 30 በቡታጅራ ከተማ፤ የደንጣ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ደግሞ ታኅሣሥ 12 በሀድያ ዞን ቢጠና ታዳጊ ከተማ የምሥረታ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ለማድረግ ሲሞክሩ ክልከላ እንደገጠማቸው ገልጿል።
የኮንቶማ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ጉባዔ፤ ቦርዱ የወከላቸው ባለሙያዎች በሕጉ መሠረት በቦታው በአካል በመገኘት ታዝበው ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተመድበው እንደነበር ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው አመልክቷል። ጉባኤው ከመደረጉ አስቀድሞም፤ የፓርቲው መሥራቾች ትብብር እንዲደረግላቸው ለክልሉ መንግሥት አስተዳደር እና በየደረጃው ላሉ የመንግስት እና የጸጥታ አካላት በደብዳቤ ማሳወቁን ቦርዱ አስረድቷል።

ሆኖም በጉባኤው ዕለት “መሣሪያ የታጠቁ” የቡታጅራ ከተማ የጸጥታ አካላት፤ “ከተማው በኮማንድ ፖስት ሥር ስለሆነች መሰብሰብ አይቻልም” በሚል ለስብሰባ የመጡ የፓርቲው መሥራች አባላትን ከአዳራሽ በማስወጣት በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸው ቦርዱ አስታውቋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጸጥታ አካላት ይህን ድርጊት የፈጸሙት፤ “ጉባዔ መደረግ የማይችልበትን ሁኔታ” በጽሑፍ ለተቋሙ ሳያሳውቁ መሆኑንም ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
በተመሳሳይ መልኩ የትብብር ደብዳቤ የተጻፈላቸው የደንጣ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሥራቾች፤ በቢጠና ታዳጊ ከተማ ጉባኤያቸውን ለማካሄድ ከተሰበሰቡ በኋላ የከተማዋ የጸጥታ አካላት “ስብሰባውን ማድረግ አይቻልም፣ የጸጥታ ድጋፍ አናደርግላችሁም” በማለት ክልከላ ማድረጋቸውን ምርጫ ቦርድ ጠቅሷል። የጸጥታ አካላቱ “ስብሰባውን ለመረበሽ የተዘጋጁ አካላት አሉ፣ አደጋ ቢደርስባችሁም ኃላፊነቱን አንወስድም፣ ቦታውን ለ’ቃችሁ ውጡ” ማለታቸውም በምርጫ ቦርድ መግለጫ ላይ ሰፍሯል።
ይህን ተከትሎም በቦታው በመገኘት የመሥራች ጉባዔውን በመታዘብ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተመድበው የነበሩ የቦርዱ ባለሙያዎች ከከተማዋ ለቀው እንዲወጡ መደረጉን ቦርዱ አክሏል። የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች በሁለቱ ፓርቲዎች ጉባዔ ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በተለያየ ደረጃ ካሉ የክልሉ አመራሮች ጋር በወቅቱ በመነገጋገር ያደረጉት ሙከራ “ሊሳካ እንዳልቻለም” ተቋሙ ገልጿል።

የፌዴራልም ሆነ የክልል የመንግሥት አካል፤ ከምርጫ ቦርድ ለሚቀርብለት ሕጋዊ ጥያቄ “ትብብር የማድረግ” እና “የማስፈጸም ግዴታ ያለባቸው” መሆኑን ቦርዱ በመግለጫው አስገንዝቧል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት አካላት በሕገ መንግሥቱ እንዲሁም በሌሎች ህጎች ለሁሉም ዜጎች የተሰጡ መብቶች “እንዳይፈጸሙ ማስተጓጎላቸው”፤ “የሀገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር የሚያጠብብ” እና “ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ተግባር” መሆኑን ቦርዱ በመግለጫው ላይ አስታውቋል።
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ላይ “ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማህበር የመደራጀት መብት አለው” ይላል። “በፖለቲካ ድርጅቶች ለመሳተፍ የሚጠየቀውን ጠቅላላ እና ልዩ የአባልነት መስፈርት የሚያሟላ ማንኛውም ሰው፤ በፍላጎቱ አባል የመሆን መብቱ የተከበረ መሆን አለበት” ሲል ሕገ መንግስቱ በተጨማሪነት ደንግጓል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ላይም “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመሆን መብት” እንዳለው ሰፍሯል። የዜጎች የመደራጀት እና የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት ዴሞክራሲያዊ መብት ላይ የሚፈጸሙ “የማስተጓጎል ተግባራት” ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት አካላት “ተገቢውን የእርምት ዕርምጃ” እንዲወስዱም ቦርዱ በመግለጫው “በጥብቅ” አሳስቧል።
ይህ ምርጫ ቦርድ መግለጫ ከመውጣቱ አንድ ቀን በፊት በፋና የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የነበሩት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ውስጥ “አማራጭ ሐሳብ አለኝ” የሚል አካል በሙሉ በነጻነት መንቀሳቀስ እንዲችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል” ብለው ነበር። አቶ አደም “በአሁኑ ወቅት ‘ሐሳብ አለኝ፣ የራሴን ፓርቲ መሥርቼ መታገል እፈልጋለሁ’ የሚል አካል ላይ እንቅፋት የሚፈጥር አካል የለም” ሲሉም ተደምጠዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያሉ ፓርቲዎች “በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ” ጥረት እንደሚደረግ የገለጹት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ችግሮች ቢፈጠሩ “በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል” ብለው ነበር። “[የፖለቲካ ፓርቲዎች] ቅሬታቸውን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በኩል ይሁን በሌሎች መንገድ ሲያቀርቡ፤ እኛ እንደ ገዢ ፓርቲ ትኩረት ሰጥተን፣ ለዚያ የሚመጥን አመራር መድበን፣ ችግሩ እንዲፈታ ለማድረግ ነው [የምንጥረው]” ብለዋል አቶ አደም በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































