በጋምቤላ ክልል “የጸጥታ ችግር ይስተዋልባቸዋል” በተባሉ አካባቢዎች ከዛሬ ጀምሮ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን የክልሉ መንግስት አስታወቀ። በእነዚህ አካባቢዎች ከተፈቀደላቸው የጸጥታ አካላት ውጪ፤ “በየትኛውም ቦታ” የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም ክልሉ አስጠንቅቋል።
ከዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 15፤ 2018 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የተነገረው የሰዓት እላፊ ገደብ፤ የክልሉ መንግስት መቀመጫ የሆነችው የጋምቤላ ከተማን እንደሚያካትት የክልሉ መንግስት አመልክቷል። በጋምቤላ ከተማ ከሁለት ሳምንት በፊት የተከሰተውን የጸጥታ አለመረጋጋት ተከትሎ ከህዳር 30 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሎ እንደነበር ይታወሳል።
ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ በሚደረግ የተሽከርካሪ እና የሰው እንቅስቃሴ ላይ ተጥሎ የነበረው ይኸው ክልከላ፤ የጸጥታ አካላትን እንደማይጨምር በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ዛሬ ይፋ የተደረገው የሰዓት እላፊም በተመሳሳይ መልኩ ለጸጥታ ስራ የተመደቡ ኃይሎችን እንደማይመለከት የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
የሰዓት እላፊው ገደቡ የተጣለው በጋምቤላ ክልል “ሰሞኑን በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት” እንደሆነም የክልሉ መንግስት በመግለጫው ጠቅሷል። ገደቡ የጸጥታ ችግር በሚስተዋልባቸዉ የክልሉ አካባቢዎች በሙሉ እንደሚተገበር የክልሉ መንግስት ቢገልጽም፤ ከጋምቤላ ከተማ ውጪ ያሉትን ስፍራዎች የትኞቹ እንደሆኑ መግለጫው በዝርዝር ሳያመልክት ቀርቷል።
መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው እሁድ ባወጣው መግለጫ፤ በጋምቤላ ክልል “ግጭት” እና “የጸጥታ መደፍረስ” የተከሰተባቸው ጋምቤላ ከተማ፣ ጋምቤላ ወረዳ (አቦል) እና ኢታንግ ልዩ ወረዳ መሆናቸውን ገልጾ ነበር። በሰሞኑ የክልል ግጭት “የሰዎች ህይወት መጥፋቱን” እና “የአካል ጉዳት” መድረሱንም ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































