አሜሪካ ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የሚውል ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ልታደርግ ነው። የገንዘብ ድጋፉ በዋናነት የወባ፣ የኤች አይ ቪ እና የቲቢ በሽታዎችን ለመከላከል እንዲሁም የእናቶች እና የህጻናትን ጤና ለመጠበቅ እንደሚውል ተገልጿል።
የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ድጋፍ፤ በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ስምምነት የተደረሰበት የጤና ትብብር ማዕቀፍ አካል ነው። ለአምስት ዓመታት የሚቆየው የእዚህ ትብብር የመግባቢያ ሰነድ (MOU) ይፋዊ የፊርማ ስነ ስርዓት ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 14፤ 2018 ተካሂዷል።
በገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው በዚህ ስነ ስርዓት ላይ የአሜሪካ መንግስትን በመወከል ፊርማቸውን ያኖሩት በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር የሆኑት ኧርቪን ማሲንጋ ናቸው። በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ እና የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ የመግባቢያ ሰነዱን ፈርመዋል።

የኢትዮጵያን የጤና ስርዓት የማሻሻል ዓላማ ያለው ይህ የሁለቱ ሀገራት የመግባቢያ ስምምነት፤ የ1.6 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ነው። ከዚህ ውስጥ አሜሪካ 1.016 ቢሊዮን ዶላሩን በድጋፍ መልክ፣ 150 ሚሊዮን ዶላሩን ደግሞ አፈጻጸምን መሰረት በማድረግ የምታቀርብ ሲሆን ቀሪው 450 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ይሆናል።
የአሜሪካ መንግስት ባለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ላይ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉን አምባሳደር ማሲንጋ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል። የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ በበኩላቸው በዚህ ስምምነት የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ በዋናነት የወባ፣ የኤች አይ ቪ እና የቲቢ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚውል ገልጸዋል።
በጤና ትብብሩ የሚገኘው ድጋፍ የእናቶች እና የህጻናትን ጤና መጠበቅ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም አስረድተዋል። በትብብሩ የሚገኘው ድጋፍ የጤና ባለሙያዎችን ብቃት እና ክህሎት ለማሳደግ እንዲሁም የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦትና ምርትን ለመጨመር የሚረዳ እንደሆነም ጠቅሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ከቆይታ በኋላ ማስተካከያ ተደርጎበታል]


































