በትግራይ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተን ሥራ በመቆሙ፤ የ67 ሰራተኞቹን የኮንትራት ውል ለማቋረጥ መገደዱን የተሃድሶ ኮሚሽን ገለጸ

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በትግራይ ክልል የሚያከናወነውን የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና የመበተን (demobilization) ሥራ ከመስከረም ወር ጀምሮ “ላልተወሰነ ጊዜ” እንደተቋረጠ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጸ። በዚህ ምክንያት በክልሉ የሚገኙ የቀድሞ ተዋጊዎችን መረጃ በዲጂታል መንገድ የሚመዘግቡ 67 ባለሙያዎችን የኮንትራት የሥራ ውል ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደሚያቋርጥም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ትጥቃቸውን የሚፈቱ ኃይሎች “ወደማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ እና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ የማድረግ” ኃላፊነት የተጣለበት ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ የተቋቋመው በህዳር 2015 ዓ.ም ነበር። ኮሚሽኑ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ መበተን እና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ ማዋሃድ (DDR) ስራ መጀመሩን በይፋ ያስታወቀው ከዘጠኝ ወራት በኋላ እንደነበር ይታወሳል።

ኮሚሽኑ በዚሁ ወቅት በሰጠው መግለጫ፤ ስራው በሰባት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን የሚሸፍን መሆኑን ገልጾ ነበር። በትግራይ ክልል ብቻ ትጥቅ ይፈታሉ ተብለው የሚጠበቁ የቀድሞ ተዋጊዎች ብዛት 274,800 እንደሆነ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ተስፋአለም ይሕደጎ፤ ከትግራይ ክልል በመጀመሪያው ዙር ትጥቅ ፈትተው እና ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ የተቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ብዛት ከ63,300 በላይ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እነዚህ የቀድሞ ታጣቂዎች ስልጠና የወሰዱት፤ በመቐለ፣ እዳጋ ሀሙስ እና አድዋ ከተሞች በሚገኙ ማዕከላት እንደሆነም ገልጸዋል። 

በመጀመሪያ ዙር የቀድሞ ታጣቂዎችን “ዲሞቢላይዝ” ለማድረግ ከተያዘው እቅድ አንጻር፤ በክልሉ 11 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ታጣቂዎች ላይ የትጥቅ ማስፈታቱ እና የመበተኑ ስራ እስካሁንም አለመከናወኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። ይህ ሥራ ማለቅ የነበረበት እስካለፈው መስከረም ወር ድረስ እንደነበርም አቶ ተስፋአለም አክለዋል።

“የፖለቲካ ትኩሳት በዚህም በዛም” መኖሩ ሂደቱን ማስቀጠል እንዳይቻል “ፈታኝ ሁኔታ” መፍጠሩን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። “ዲሞቢላይዝ” ለማድረግ አመራሮቹም፣ ታጣቂዎቹም “ፈቃደኛ ሆነው መምጣት ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ ሂደቱ ለምን እንደተቋረጠ አብራርተዋል። 

በትግራይ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎችን “እንደ አዲስ ሞቢላይዝ የማድረግ ምልክቶች አሉ” ያሉት አቶ ተስፋአለም፤ ሂደቱ የተቋረጠበት አንዱ ምክንያት “እሱን በማጣራት እና ግልጽ አድርጎ በድጋሚ ወደ ሥራ ለመመለስ” በማሰብ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር “ቴክኒካዊ ጉዳዮችን” “ቶሎ መፍታት ባለመቻሉ” ሂደቱ ከመስከረም ወር ጀምሮ መቋረጡንም አክለዋል። 

የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት እና የመበተን ሂደት በተመሳሳይ ምክንያት በትግራይ ክልል ሲቋረጥ የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም። ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ባወጣው መግለጫ፤ በክልሉ የነበረው ሂደት “በአንዳንድ ቴክኒካዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች” ተቋርጦ መቆየቱን ገልጾ ነበር። 

ኮሚሽኑ ከየካቲት 2017 ዓ.ም በኋላ ባሉት አራት ወራት ውስጥ ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል አቅዶ የነበረው የቀድሞ ተዋጊዎች ብዛት 67 ሺህ ነበር። መስሪያ ቤቱ የ2018 በጀት ዓመት ሶስት ወራት አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት ባሰራጨው መረጃ፤ “በሩብ ዓመቱ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች ከ20 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በDDR ፕሮግራም ተሳትፈው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጋቸውን” አስታውቆ ነበር።

ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ይህን መረጃ ያወጣው ባለፈው ጥቅምት ወር ቢሆንም፤ በትግራይ ክልል ሲካሄድ የቆየው “የዲሞብላይዜሽን” ስራ ያቋረጠው ግን ከመስከረም ወር ጀምሮ መሆኑን የመስሪያ ቤቱ ምክትል ኮሚሽነር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ኮሚሽኑ ለዚሁ ስራ ለቀጠራቸው የኮንትራት ሰራተኞች ባለፈው ሐሙስ ታኅሣሥ 16፤ 2018 በጻፈው ደብዳቤም፤ በክልሉ የነበረው “የዲሞብላይዜሽን” ስራ “ላልተወሰነ ጊዜ” መቋረጡን ገልጿል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይኸው ደብዳቤ፤ በዚሁ ምክንያት በትግራይ ክልል የሚገኙ የቀድሞ ተዋጊዎችን በዲጂታል መንገድ የሚመዘግቡ ባለሙያዎች “የኮንትራት ውል” ከጥር 1፤ 2018 ጀምሮ ጀምሮ “የተቋረጠ” መሆኑን ይገልጻል። ውሉ የተቋረጠው “ምንም ስራ በሌለበት ደመወዝ መክፈል በሲቪል ሰርቪስ አሰራር እና ህግ መሰረት የማይፈቅድ” በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ በደብዳቤው ላይ ሰፍሯል።

ኮሚሽኑ የባለሙያዎቹን የሥራ ውል የማቋረጥ ውሳኔ ላይ የደረሰው ያለ ሥራ ደመወዝ መክፈል “የፋይናንስ ተጽዕኖ” ስለሚኖረው እንደሆነ አቶ ተስፋአለም ተናግረዋል። ኮሚሽኑ እስካሁን በሀገሪቱ ላከናወነው የDDR ሥራ 6.7 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ገንዘቡ የተገኘው በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (UNDP) በኩል ባሉ ለጋሽ ሀገራት መሆኑን አመልክተዋል።  

ከዚህ በተጨማሪ የፌደራል መንግሥት ለአልባሳት፣ ለቀለብ እና ለስልጠና እና ሌሎች ወጪዎች የሚውል 2 ቢሊዮን ብር ወጪ እንዳደረገም አቶ ተስፋአለም አክለዋል። እያንዳንዱ የቀድሞ ተዋጊ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀል 90,400 ብር ወደ ባንክ ሂሳብ ቁጥሩ ገቢ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን ላለፈው አንድ ዓመት በዲጂታል መንገድ ሲመዘግቡ የነበሩት ባለሙያዎች ቁጥር 67 እንደሆነ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ኮሚሽኑ የእነዚህን ባለሙያዎች የኮንትራት ውል ያቋርጥ እንጂ፤ አሁንም በስልጠና ማዕከላት ውስጥ ያሉ ሰራተኞች መኖራቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

“አሁን በማዕከላቱ ሙሉ በሙሉ ሥራ አቋረጥን ማለት አይደለም። የመዝጋቢዎችን ውል ነው ያቋረጥነው” ሲሉ ተናግረዋል። የባለሙያዎቹ የስራ ውል የተቋረጠው፤ የፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ሂደትን አስመልክቶ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካነሳው ቅሬታ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የተጠየቁት ምክትል ኮሚሽነር ተስፋአለም፤ “በጭራሽ አይገናኝም” ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። 

የትግራይ ክልል ስታቲስቲክስና ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ፤ የአማራ ክልል የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሳባቸው አካባቢዎች ላይ ሲካሔድ በነበረው የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ “የክልሉን ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው” በሚል ቅሬታ አቅርቦ ነበር። የቀድሞ ታጣቂዎችን “ዲሞቢላይዝ” የማድረጉ ሥራ መቋረጥ ከፋይዳ መታወቂያ ጉዳይ ጋር እንደማያያዝ አጽንኦት የሰጡት አቶ ተስፋአለም፤ ሥራውን የማስቀጠል ሂደቱ የሚወሰነው በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፈቃደኝነት መሆኑን ገልጸዋል። 

“ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይጀመር ካለ እና መሟላት ያለባቸውን ቴክኒካዊ ጉዳዮች በማሟላት “ኃላፊነቱን ከተወጣ” ሂደቱ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ሂደቱን ለማስቀጠል ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር “ንግግር እያደረገ” ስለመሆኑም አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)