የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ከ40 በላይ መንግስታዊ የልማት ድርጅቶችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፤ አዲስ የሙስና ጥቆማ መቀበያ ስርዓት ማዘጋጀቱን ይፋ አደረገ። ይህ ስርዓት ማንኛውም ግለሰብ ባለበት ሆኖ ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መልኩ ጥቆማ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።
“አደራ” የሚል ስያሜ ያለው የሙስና ጥቆማ መስጪያ ስርዓት በአሁኑ ወቅት በድረ ገጽ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በቅርቡ ወይም በሞባይል መተግበሪያ (አፕልኬሽን) መልኩ ለተገልጋዮች ይቀርባል ተብሏል። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሰራተኞች እንደለማ የተነገረለት ይህን ድረ ገጽ ተጠቅሞ፤ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ጥቆማዎችን ማቅረብ እንደሚቻል መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
በቀጣይ ግን በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ቋንቋዎች የሙስና ጥቆማዎችን መስጠት እንደሚቻል መስሪያ ቤቱ ዛሬ ሐሙስ ታኅሣሥ 23፤ 2018 በሰጠው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል፤ ይህንን የጥቆማ መስጫ ስርዓት መዘርጋት ያስፈለገው፤ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ሙስና እንዳይፈጸም እና ከተፈጸመ ደግሞ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሁሉም የመንግስት የልማት ድርጅቶቸ የራሳቸው የሆነ ውስጣዊ አሰራር፣ የኦዲት ሪፖርት እና ሌሎች የቁጥጥር ስርዓት ቢኖራቸውም፤ የበለጠ ተጠያቂነትን ለማስፈን አዲስ የሙስና ጥቆማ መስጫ ስርዓት መዘርጋቱን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል። አዲሱ ስርዓት የልማት ድርጅቶችን ሀብት የማስመለስ አቅማቸውን ከማሳደጉ ባሻገር፤ ሙስና እንዳይፈጸም በማድረግ የተቋማቱን የመፈጸም አቅም እንደሚጨምረውም አቶ ሀብታሙ አክለዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከዚህ በፊት በእዳ፣ በውጤታማነት ማነስ እና በብልሹ አሰራር ችግሮች ሲፈተኑ የቆዩ መሆናቸውን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከተቋቋመባቸው አላማዎች አንዱ እነዚህን መሰል አሰራሮች እንዳይደገሙ እና የተቋማቱን ውጤታማነት ለማሳደግ መሆኑንም አስረድተዋል።
በልማት ድርጅቶች ውስጥ “ተጠያቂነትን ለማስፈን” ይረዳል የተባለውን አዲሱን ድረ ገጽ በመጠቀም የሚላኩ የሙስና ጥቆማዎችን የሚያዩት፤ “የተቋሙ ጥቂት ከፍተኛ አመራሮች ብቻ እንደሆኑ” በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። ጥቆማዎቹን ለዚህ ዓላማ ተብሎ የሚዘጋጅ ቡድን፤ ወደሚመለከታቸው አካላት እንደሚልክም ተመልክቷል።

መጠቆሚያ ድረገጹ ጠቋሚዎች ማስረጃ እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ መሆኑን በማንሳት፤ “አንዳንድ የሙስና ጥቆማዎች ማስረጃ ላይኖራቸው ስለሚችል ይህን እንዴት ልትፈቱት አስባችኋል?” የሚል ጥያቄ በመግለጫው ላይ ተነስቷል። “ይህ የተደረገው ትክክለኛ የሙስና ጥቆማዎችን መስጠት የሚችሉ ሰዎች ችግር እንዳይገጥማቸው እና ሁሉም ሰው ወደ ድረ ገጹ እየመጣ አሉባልታዎችን እንዳይጠቁም በሚል ነው” ሲሉ በመስሪያ ቤቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር እስማኤል ከድር ምላሽ ሰጥተዋል።
በመንግስት የልማት ድርጅቶች የብልሹ አሰራር እና የሙስና ጥቆማ መስጫ የዲጂታል ስርዓት ይፋ ሲደረግ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር ካሉ የመንግስት ልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፤ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ይህንኑ አገልግሎት የሚሰጥ የሞባይል መተግበሪያ አስተዋውቆ ነበር።
የሞባይል መተግበሪያውን ስራ ላይ ማዋል ያስፈለገው፤ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚቀርቡ አገልግሎቶች ላይ የሙስናና ብልሹ አሰራር ቅሬታዎች ሲኖሩ ደንበኞች ቅሬታቸውን በቀላሉ ማቅረብ እንዲችሉ ለማድረግ በሚል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። “EEU Anti-corruption” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ መተግበሪያ፤ ደንበኞች ለሚያቀርቡት ጥቆማ ማስረጃ የሚሆኑ የምስል ፣ ቪዲዮ እና የፅሁፍ ሰነዶችን መጫን የሚያስችል ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































