“የቤት ባለቤት እናደርጋችኋለን” በሚል ባለፈው ዓመት ከሕዝብ ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ “ያጭበረበሩ” ሰዎች መከሰሳቸውን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ። እንደዚህ አይነት “ማጭበርበር” በሚፈጽሙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምክንያት፤ ዜጎች “ገንዘብ ይዘው እንኳን ያለ ስጋት ቤት ለመግዛት እየተቸገሩ” መሆኑን አንዲት የፓርላማ አባል ተናግረዋል።
አፀደ ማሞ የተባሉት እኚሁ የፓርላማ አባል፤ በሀገር ደረጃ “ከፍተኛ ትኩረት” ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ካሉ ጉዳዮች ውስጥ “የዜጎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ” አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል። ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ከአማራ ክልል ዳባት ምርጫ ክልል የተመረጡት የፓርላማ አባሏ፤ “ ‘ቤት ሰርተን እንስረክባለን’ በማለት የህዝብን ገንዘብ ሰብስበው ከሀገር የሚወጡ” የግል ድርጅቶች እንዳሉ ገልጸዋል።
በቤት ልማት ዘርፍ ከተሰማሩ የግል ድርጅቶች ውስጥ “በውላቸው መሰረት በጊዜ ሰርተው የማያስረክቡ”፣ “ሰነድ የሚያጨበርብሩ” እና “በጣም ውስብስብ የሆነ ሰነድ በማስፈረም በየጊዜው ያለ ምክንያት ገንዘብ የሚጨምሩ” እንዳሉ ወ/ሮ አፀደ አስረድተዋል። እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ሲቀርቡ፤ “የህዝብን ጥቅም ከማስጠበቅ” እና “ፍትህ ከማስፈን” አንጻር ፍትሕ ሚኒስቴር ምን እየሰራ እንደሆነም የፓርላማ አባሏ ጠይቀዋል።
የፓርላማ አባላትን ጥያቄ ለመመለስ ዛሬ ሐሙስ ታኅሣሥ 23፤ 2018 በተካሔደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት የፍትህ ሚኒስትሯ ሃና አርዓያሥላሴ፤ ከህዝብ ንብረት ሰብስበው ከዳር ሳያደርሱ “የሚሰወሩ እና የሚጠፉ አካላትን በተመለከተ የወንጀል ተጠያቂነትን እያሰፈንን እንገኛለን” ብለዋል። “የቤት ባለቤት እናደርጋችኋለን” በሚል ከህዝብ ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ “በሰፊው የማጭበርበር ስራ ላይ የተሰማሩ” ያሏቸው ሰዎች ላይ መስሪያ ቤታቸው ባለፈው ዓመት ክስ መስርቶ፤ ጉዳዩ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































