በሀዋሳ እና ደብረ ብርሀን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ ፋብሪካዎች ከእነ ማሽኖቻቸው ለጨረታ ቀረቡ 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሀዋሳ እና ደብረ ብርሀን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ የማምረቻ ሼዶችን ለሶስተኛ ወገን ለማስተላለፍ ጨረታ አወጣ። ኮርፖሬሽኑ  ፋብሪካ ሼዶቹን በውስጣቸው ካሉ ማሽኖች እና ንብረቶች ጋር ጨረታ ያወጣባቸው፤ ማምረቻዎቹ “በተለያዩ ምክንያቶች ምርት በማቆማቸው” እንደሆነ ገልጿል። 

ከመንግስት ግዙፍ የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፤ በሀዋሳ እና ደብረ ብርሀን የሚገኙትን ጨምሮ 10 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በስሩ የሚያስተዳድር ነው። በ2006 ዓ.ም የተመሰረተው ኮርፖሬሽኑ፤ በድሬዳዋ የሚገኘውን እና ከሶስት ዓመት በፊት የተመረቀውን ነጻ የንግድ ቀጠና የማስተዳደር ኃላፊነትም ተጥሎበታል።

የካፒታል መጠናቸው ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ፣ ከ50 ሄክታር  በላይ የቆዳ ስፋት ያላቸውን እና ሌሎች መስፈርቶችን ያሟሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፤ ኮርፖሬሽኑ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንነነት ያሳደገው በህዳር 2017 ዓ.ም ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንንነት ማደግ፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ “ፋይዳው ከፍተኛ ነው” ተብሎ ነበር። 

ይህንን ደረጃ ካገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ በሆነው የሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ካሉ አምራቾች መካከል በስምንቱ ላይ ኮርፖሬሽኑ  ጨረታ አውጥቶባቸዋል። ኮርፖሬሽኑ ጨረታውን ያወጣው፤ ከተቋሙ ጋር ውል የገቡ አምራቾች በውላቸው መሰረት ማምረት ባለመቻላቸው ምክንያት እንደሆነ የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ በለጠ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

አምራቾቹ ወደ ስራ እንዲገቡ በተደጋጋሚ ጥረት መደረጉን የገለጹት አቶ ጳውሎስ፤ ይህ ባለመሳካቱ ማምረቻ ቦታዎቹ (ሼዶች)፣ ማሽኖች እና መሰል ንብረቶች ለሶስተኛ ወገን በጨረታ ለማስተላለፍ ተቋሙ መወሰኑን ገልጸዋል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ የማምረቻ ሼዶችን በጨረታ ለአምራቾች የማስተላለፍ ውሳኔ ሲተላለፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነም አክለዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ጨረታ የወጣባቸውን የማምረቻ ቦታዎች ተረክበው የነበሩ አምራቾችን ስም እና ውል የገቡባቸውን ጊዜያት ከመናገር ቢቆጠቡም፤ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የጨረታ ማስታወቂያ ግን በሀዋሳ ለጨረታ የቀረቡ 10 የፋብሪካ ሼዶች፤ ቲ ሸርት፣ ሸሚዝ፣ ፓካውት፣ የውስጥ ልብስ፣ ጡት ማስያዣ፣  ፓንት፣ ካልሲ እና የህጻናት ዳይፐር የሚያመርቱ እንደሆኑ ይገልጻል። 

እነዚህን ምርቶችን ለማምረት የተዘጋጁት የፋብሪካ ሼዶች አጠቃላይ ስፋት 52,500 ካሬ ሜትር እንደሆነ ባለፈው ሰኞ ታህሳስ 20፤ 2018 የወጣው የጨረታ ማስታወቂያ ያሳያል። ጠቅላላ ስፋታቸው 11,000 ካሬ ሜትር የሆኑት እና በደብረ ብርሃን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የሚገኙት ቀሪዎቹ ሁለት የፋብሪካ ሼዶች፤ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት የሚመረቱባቸው ነው።

በደብረ ብርሃን እና ሀዋሳ የሚገኙ እነዚህን ማምረቻዎች ለመረከብ የሚፈልጉ ተጨራቾች በ15 ቀናት ውስጥ መመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል። ለኢትዮጵያዊያን እና የውጭ ዜጎች ክፍት በተደረገው በዚህ ጨረታ ላይ የሚሳተፉ ተጫራቾች፤ “የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችን መስፈርት” ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው ኮርፖሬሽኑ አመልክቷል። ተጫራቾቹ “ለማምረት ዝግጁ” መሆን እንደሚገባቸውም ተቋሙ በማስታወቂያው ላይ አስፍሯል። 

ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶችን በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ለማምረት፤ በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ከታቀደው ውስጥ ማሳካት የተቻለው 53 በመቶ ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን  ባለፈው ህዳር ወር ላይ ገልጾ ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን በተመረቱ ተኪ ምርቶች ማዳን የተቻለው የገንዘብ መጠን 211 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ በፓርላማ ጥያቄ ማስነሳቱ ይታወሳል።

በሩብ ዓመቱ ከልዩ ኢኮኖሚ ዞን ኤክስፖርት ከተደረጉ ምርቶች የተገኘው የገንዘብ መጠን 49.8 ሚሊዮን ዶላር መሆኑም ባለፈው ወር በነበረው የፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተገልጿል።  ይህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሰጥታው የነበረውን ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ ለመላክ የሚያስችል መብት (አጎዋ) ማቆሟን ለማካካስ በተወሰደ እርምጃ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በወቅቱ አስታውቋል። 

አሜሪካ ኢትዮጵያን ከ“አጎዋ” ተጠቃሚነት በጥቅምት 2014 ዓ.ም. የሰረዘችው፤ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ጦርነት ወቅት “በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸውን ሰብዓዊ መብቶች በመተላለፍ ከፍተኛ ጥሰት ፈጽሟል” በሚል ነበር። ከ“አጎዋ” የንግድ ተጠቃሚነት መቆም በኋላ “የኤክስፖርት መቀዛቀዝ ታይቶ” እንደነበር ኮሚሽኑ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት ላይ አምኗል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)