ፍትሕ ሚኒስቴር በአማራ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ላይ “ማስረጃ ማቅረብ ካልቻለ” ክሱን “እንዲያቋረጥ” ተጠየቀ

የፍትሕ ሚኒስቴር በ‘ማንነታቸው’ እና በ‘ፖለቲካ አመለካከታቸው’ የታሰሩ የአማራ ክልል ተወላጅ እስረኞች ላይ ማስረጃ ማቅረብ ካልቻለ፣ ክሱን “እንዲያቋርጥ” ተጠየቀ። ከሁለት ዓመት በላይ የታሰሩ “የአማራ ክልል ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ አንቂዎች እና የሃይማኖት አባቶች” ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚጠበቅበትን የሰነድ፣ የሰው ማስረጃ እና ምስክር “ማቅረብ ባለመቻሉ”፤ ተከሳሾቹ ለከፍተኛ የሰብዓዊ ጉዳት መዳረጋቸው ተገልጿል።

ጥያቄውን ዛሬ ሐሙስ ታህሳስ 23፤ 2018 በተካሄደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ያነሱት፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው ፓርላማውን የተቀላቀሉት ዶ/ር አበባው ደሳለው ናቸው። ፍትሕ ሚኒስቴር ክስ የመመስረት እና በሕግ አግባብ መከናወኑን በመከታተል አፋጣኝ ፍትሕ ለዜጎች ማዳረስ የሥራው አካል መሆኑን የፓርላማ አባሉ ጠቁመዋል። 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “ማስረጃ እና ምስክር ማቅረብ ካልቻለ” “የተሰጠውን ክስ የማቋረጥ ሥልጣን መጠቀም ሲገባው ታሳሪዎች በፍትሕ መጓደል የሚሰቃዩት እስከመቼ ነው?” ሲሉ ዶ/ር አበባው ጠይቀዋል። የፓርላማ አባሉ አያይዘውም፤ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በሚገኙ እስረኞች ላይ “በሚያጋጥም” የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ዳኞች ፍርድ ቢሰጡም፤ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ይህንን ትዕዛዝ “ተቀብለው እንዳማይተገብሩት” ገልጸዋል።

ለዚህም እንደ አብነት “የአማራ የሕሊና እስረኞች” “የማረሚያ ቤት ዋና ኃላፊ ሰብስቦን ‘አጸያፊ ብሔር ተኮር ስድብ ሰድቦናል፣ የግድያ ዛቻ ዝቶብናል’ ” በማለት ክስ ማቅረባቸውን አንስተዋል። ተከሳሾቹ ከዚህ በተጨማሪም “ከማደሪያ ክፍል እያወጡ ይደበድቡናል” የሚል ክስ ጭምር ቢያቀርቡም፤ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ችግሩን መቅረፍ እንዳልቻሉ የፓርላማ አባሉ አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቶች ለፌደራል ፖሊስ ጉዳዩን እንዲመረምሩ እና ሪፖርት እንዲያቀርቡ ቢጠይቁም፣ ከወራት በላይ ፖሊስ ሪፖርት ማቅረብ እና ችግሩ መቀረፍ አለመቻሉን ጨምረው ገልጸዋል። “ይኽንን እና መሰል የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚሠሩ የፌደራል ማረሚያ ቤት አመራሮች ላይ ተጠያቂነት የምታሰፍኑት መቼ ነው? ይህንን ለማስተካከል ምን እየሠራችሁ ነው?” ሲሉ ዶ/ር አበባው በዛሬው ስብሰባ ላይ የተገኙትን የፍትሕ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጠይቀዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉን አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ክስ ከመሠረተባቸው በኋላ፤ “የፍርድ ሂደቱ ዘግይቷል” በሚል ተመሳሳይ አቤቱታዎች ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የፓርላማ ስብሰባዎች ላይ  መቅረባቸው የሚታወስ ነው። ይህ እና በእስረኞቹ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፓርላማ በተገኙባቸው ስብሰባዎች ላይ ጭምር ሲያነጋግሩ ቆይተዋል። 

በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሀና አርዓያሥላሴ፤ “በማንነቱ ብቻ ወይም በፖለቲካ አቋሙ ብቻ የከሰስነው ወይም ፍርድ ቤት ያቆምነው ሰው የለም” ሲሉ አስተባብለዋል። የፍርድ ሂደቱ በሚፈልገው “ቅልጥፍና ላይ” አለመድረሱን እና “ትኩረት የሚሻ” መሆኑን ያመኑት ሚኒስትሯ፤ “በተለይ የወንጀል ምርመራ ሂደታችን ላይ የተሻለ ቅልጥፍና እንዲመጣ ሰፊ ሥራዎች እየሠራን ነው” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። 

በክስ ሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮች በሙሉ “ሕገመንግሥቱን እና ሕገመንግሥታዊ ስርዓቱን” እንዲሁም ሌሎች ሕጎችን ማስጠበቅ ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ ሚኒስትሯ ጨምረው ገልጸዋል። “አንድ ሰው የፖለቲካ ግቡን ለማሳካት በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ፖለቲከኛም ሆነ የመንግስት ሰራተኛም ሆነ ኃላፊ ተጠያቂነትን እናረጋግጣለን” ያሉት ሚኒስትሯ፤ “የትኛውም ሰው” ከህግ በታች እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የፍትሕ ሚኒስትሯ የሽብር እና ተመሳሳይ ውስብስብ ወንጀሎች ላይ የሚደረጉ ክርክሮች “ረጅም ጊዜ” እንደሚወስዱ ግን አልሸሸጉም። “ጉዳዩም ውስብስብ ስለሆነ ብዙ ምስክሮች የሚጠሩበት እና ሰነዶች የሚቀርቡበት ነው። ከመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ጀምሮ በእያንዳንዱ ጭብጥ ላይ ክርክር ተደርጎ ብይን የሚሰጥበት ነው” ሲሉም ሂደቱ ጊዜ የሚወስድ መሆኑን አብራርተዋል።

የወንጀል ተጠያቂነት ማረጋገጥ ከባድ ሥራ መሆኑን ለፓርላማ አባላቱ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በወንጀል ጥፋተኛ ለማስባል መቶ በመቶ የተጠጋ እርግጠኝነት እና የማስረዳት ሸክም እንዳለው አስረድተዋል። ሂደቱ ከባድ ቢሆንም በክስ እና በክርክር ሂደቶች ወቅት “ምስክር ሳይቀርብ የተቋረጠም ይሁን የተጓተተ ጉዳይ እንደሌለ” ወ/ሮ ሀና ተናግረዋል። 

ከፓርላማ አባላት ለሚቀርቡላቸው የቃል ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የዛሬውን የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የታደሙት የፍትሕ ሚኒስትሯ፤ የማረሚያ ቤቶች ጉዳይንም በማብራሪያቸው ዳስሰዋል። በፌዴራልም ሆነ በክልል ያሉ ማረሚያ ቤቶች “በጣም ሰፊ” የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የተመለከቱ “ጥያቄዎች” ይነሱባቸው እንደነበር ወ/ሮ ሀና ለፓርላማ አባላቱ አስታውሰዋል።

ባለፉት ዓመታት መሠረታዊ ለውጥ ከተደረገባቸው ተቋማት ውስጥ የማረሚያ ቤቶች እንደሚገኙበት ሚኒስትሯ በምላሻቸው ጠቅሰዋል። ከለውጦቹ መካከል “በተቻለ” እና “አቅም በፈቀደ” መንገድ ተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች በምቹ ሁኔታ ውስጥ እንዲጠበቁ ማድረግ የሚያስችል መሠረት ልማት መገንባት አንዱ መሆኑንም አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር ተያይዞ ጥያቄዎችን እንደሚያነሱ ሚኒስትሯ አልሸሸጉም። ለእነዚህ ጥያቄዎች ፍርድ ቤቶች “የግራ ቀኙን” አቤቱታ እና ምላሽ በመስማት “ተገቢውን ውሳኔ” እንደሚሰጡ ተናግረዋል። በፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔዎችም በማረሚያ ቤት “በተቻለ መጠን” እንደሚተገበሩ አስረድተዋል።

በእስር ላይ ያሉ ታራሚዎችም ሆነ ተጠርጣሪዎች “ያልተገደበ መብት እንደሌላቸው” ታሳቢ መደረግ እንዳለበት ያስገነዘቡት ሚኒስትሯ፤ “መብታቸውን እንደሚጠይቁት ሁሉ ግዴታቸውን የመወጣት ኃላፊነት አለባቸው” ሲሉ ተደምጠዋል። ሚኒስትሯ በታራሚዎች በኩል ይደረጋሉ ያሏቸው “ሕገ ወጥ” እንቅስቃሴዎች፤ በማረሚያ ቤት ላይ “ትልቅ ሸክም” እንደሆኑ ለፓርላማ አባላት ገልጸዋል።

ወደ ማረሚያ ቤት “የተከለከሉ ነገሮች ይዞ መግባት” እና “የማምለጥ ሙከራዎች”፤ በዚህ አውድ ውስጥ ሊታይ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። ታራሚዎችን በተመለከተ በአጠቃላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በጉዳዩ ላይ ክትትል እንደሚያደርግ ሚኒስትሯ ገልጸዋል። 

ባለፈው በጀት ዓመት “በተደጋጋሚ የተጎበኙትንም ጨምሮ” 170 ሺህ የሚጠጉ ታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች በዐቃብያነ ሕግ መጎብኘታቸውን ወ/ሮ ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። በእነዚህ ጉብኝታቸው ወቅት ዐቃብያነ ሕግ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መፍትሔ እንዲያገኙ እና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የማድረግ ጉዳዮችን እንደሚመለከቱም ሚኒስትሯ ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)