የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ትላንት አመሻሽ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ባለቤታቸው ተናገሩ  

የጋምቤላ ክልል ፖሊስን በኮሚሽነርነት የሚመሩት አቶ ኡጉላ ኡጁሉ ትላንት አመሻሹን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ አርያት ኡባንግ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የፌደራል ፖሊስ አባላት በጋምቤላ ከተማ ያሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ትላንት ሐሙስ በተንቀሳቀሱበት ወቅት፤ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በጋምቤላ ከተማ ባለ አንድ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ የከተማይቱ ነዋሪ፤ ትላንት ከእኩለ ቀን በኋላ በፌደራል ፖሊስ ተሽከርካሪዎች ሰዎች ታስረው ሲወሰዱ መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ከታሰሩት ሰዎች ውስጥ በክልሉ ባሉ የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ እና የጸጥታ ኃይሎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት፤ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር እኚሁ ነዋሪ ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሌላ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪም ይህንኑ አረጋግጠዋል። የተኩስ ድምጹ በዛሬው ዕለት እንደቆመ ሁለቱም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በትላንትናው ዕለት በፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከል የጋምቤላ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኡጉላ እንደሚገኙበት ባለቤታቸው ወ/ሮ አርያት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ ኡጉላ በፌደራል ፖሊስ አባላት ተይዘው ወደ ቤታቸው ለፍተሻ ከመወሰዳቸው አስቀድሞ በጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነበሩ ተብሏል።

በጋምቤላ ከተማ ስድስት ኪሎ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደሚገኘው የፖሊስ ኮሚሽነሩ መኖሪያ ቤት የሄዱ የፌደራል ፖሊስ አባላት በአራት ተሽከርካሪዎች የተጫኑ እንደነበሩ የአቶ ኡጉላ ባለቤት ገልጸዋል። የጦር መሳሪያ የታጠቁት ፖሊሶች በቤታቸው ፍተሻ ካደረጉ በኋላ፤ ለኮሚሽነሩ ከመንግስት የተሰጣቸውን ሽጉጥ ይዘው እንደሄዱ ባለቤታቸው አስረድተዋል።

የፌደራል ፖሊስ አባላቱ አቶ ኡጉላን ወደ ቤት ሲያመጧቸውም ሆነ በፍተሻ ወቅት “አካላዊ ጥቃት እንዳልፈጸሙባቸው” የገለጹት ወ/ሮ አርያት፤ ፍተሻው ተጠናቅቆ ባለቤታቸውን መልሰው ይዘዋቸው የሄዱት ለ12 ሰዓት ሩብ ጉዳይ ገደማ እንደነበር ተናግረዋል። ይሁንና የፖሊስ አባላቱ ባለቤታቸው ወደየት እንደወሰዷቸው እና እስካሁንም ያሉበትን እንደማያውቁ አስረድተዋል። 

በጋምቤላ ክልል የፖሊስ ኃላፊዎች በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ሲውሉ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ከሶስት ዓመት በፊት የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን ሲመሩ የነበሩት አቶ አቡላ ኡባንግ እና ምክትላቸው አቶ ቱት ኮር ጨምሮ 12 የጸጥታ ዘርፍ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ነበር። 

ሁለቱ የፖሊስ ኃላፊዎች የታሰሩት፤ የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) እና የ“ኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች ባለፈው ዓመት በሰኔ 2013 ዓ.ም ወር በጋምቤላ ከተማ የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ በተወሰዱ እርምጃዎች “እጃቸው አለበት” በሚል ነበር። የፍትሕ ሚኒስቴር የቀድሞውን የክልሉን የፖሊስ ኮሚሽነር ጨምሮ በ14 አመራሮችን እና ፖሊሶች ላይ በግንቦት 2015 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መመስረቱም የሚታወስ ነው። 

በትላንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ኡጉላ፤ የጋምቤላ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊነትን የተረከቡት ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ነበር። የአቶ ኡጉላን እስር በተመለከተ ከክልሉ ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

በጋምቤላ ክልል ካለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ በተከሰተው “የጸጥታ መደፍረስ” እና “ግጭት”፤ ቁጥራቸው በወል ያልታወቀ ሰዎች “ህይወት መጥፋቱን” እና “የአካል ጉዳት መድረሱን” የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ታህሳስ 12፤ 2018 ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። በዚህ ወቅት ከተገደሉት መካከል የጋምቤላ ከተማ የፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር አቶ ኡሙድ ኡጁሉ ይገኙበታል። 

የከተማይቱ የፖሊስ አዛዥን መገደልን ተከትሎ የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠር፤ የክልሉ መንግስት በጋምቤላ ከተማ እና “የጸጥታ ችግር ባለባቸው” አካባቢዎች የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉ ይታወቃል። ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ የሚቆየው የሰዓት እላፊ ገደብ፤ በጋምቤላ ከተማ “አንጻራዊ ሰላም” ማምጣቱን ነዋሪዎች ከቀናት በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር። 

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድም በክልሉ አንጻራዊ መረጋጋት መስፈኑን እና ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው “እየተመለሱ መሆኑን” ከትላንት በስቲያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመሳሳይ ገልጸው ነበር። በአሁኑ ወቅት የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ አጠቃላይ የክልሉን “ሰላም እያስጠበቁ” የሚገኙት በዋናነት የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደሆኑም ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች፤ የፌደራል ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ መውሰድ የጀመረው የእስር እርምጃ “ተገቢ ነው” የሚል እምነት አላቸው። በጋምቤላ ክልል የሚከሰቱ ግጭቶች ለመደጋገማቸው አንዱ ምክንያት “ተጠያቂነት አለመስፈን” መሆኑን አንድ የከተማይቱ ነዋሪ ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር በተያያዘ ምን ያህል ተጠርጣሪዎች እንደተያዙ ከትላንት በስቲያ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ “አሁን ግጭቱን የማረጋጋት ስራ ነው እየሰራን ያለነው። የተያዘም ካለ የሚነገርበት ሰዓት አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። ሆኖም “ለጸጥታ ችግሩ ምክንያት ናቸው” በተባሉ ግለሰቦች ላይ “በጥናት ላይ የተመሰረተ” እርምጃ እንደሚወሰድ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)