በመተሐራ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ፈንታሌ ተራራ ላይ እሳት መታየቱን ተከትሎ፤ ከትላንትና ጀምሮ ይህንኑ የሚያሳይ ፎቶዎች በማህበራዊ ብዙሃን መገናኛዎች ያጋሩ ግለሰቦች ክስተቱ “የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ” እንደሆነ ሲገልጹ ተስተውለዋል። ሆኖም በተራራው ላይ የተከሰተው ቃጠሎ፤ እንደተባለው በእሳተ ገሞራ የተከሰተ ሳይሆን በሰዎች የተስፋፋ ሰደድ እሳት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ፈንታሌ ተራራ በአፋር ክልል፣ ገቢ ረሱ ዞን፣ አዋሽ ፈንቲዓሌ ወረዳ እና በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ፈንታሌ ወረዳ መካከል የሚገኝ ነው። የፈንታሌ እና በአቅራቢያው የሚገኘው ዶፋን ተራሮች፤ በአካባቢው በተደጋጋሚ ለተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች መነሻ እንደነበሩ የዘርፉ ባለሙያዎች በወቅቱ መግለጻቸው ይታወሳል።
ንዝረታቸው አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም ጭምር ይሰማ የነበረው እነዚህ የመሬት መንቀጥቀጦች፤ በሬክተር ስኬል የተለካ መጠናቸው እስከ 6.0 ድረስ የደረሰ ነበር። በመሬት መንቀጥቀጦቹ ሳቢያ በአፋር እና ኦሮሚያ ክልል ያሉ መኖሪያ ቤቶች እና ተቋማት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
በአፋር ክልል ለመጨረሻ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ እንደሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦችን ከሚመዘግበው ከ“ቮልካኖ ዲስከቨሪ” ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ሆኖም በፈንታሌ ተራራ ላይ ከአርብ ታህሳስ 24፤ 2018 ጀምሮ ቃጠሎ መከሰቱን ተከትሎ፤ ከስተቱን ከእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ጋር ያያዙት አሉ።
ይሁን እንጂ ክስተቱ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ውጤት ሳይሆን በሰዎች አማካኝነት የተቀሰቀሰ እና የተስፋፋ ሰደድ እሳት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአፋር ክልል፣ የአዋሽ ፈንቲዓሌ ወረዳ ዛሬ እሁድ ከሰዓት ባሰራጨው መረጃም፤ በፈንታሌ ተራራ ላይ የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ (ቮልካኖ) የተከሰተ እንዳልሆነ አረጋግጧል።
የአዋሽ ፈንቲዓሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደን በላእን ዋቢ ያደረገው የወረዳው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት፤ የእሳት ቃጠሎው የተነሳው በኦሮሚያ ክልል፣ ፈንታሌ ወረዳ፣ በመተሐራ ከተማ አቅራቢያ በኩል ባለው የተራራው ክፍል መሆኑን አስታውቋል። ይህንኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት ኢብራሂም ሃጂ አህመድ የተባሉ የመተሐራ ከተማ ነዋሪ፤ እሳቱ የተከሰተው ከትላንት በስቲያ አርብ ታህሳስ 24፤ 2018 ከሰዓት በኋላ እንደነበር ገልጸዋል።

ነዋሪው “በሰው ንክኪ የተቀሰቀሰ ነው” ያሉት ይህ የእሳት ቃጠሎ፤ በተራራው ላይ ባሉ “የደረቁ ሳሮች” እገዛ ወደ ሰደድ እሳትነት መቀየሩን ያስረዳሉ። እሳቱ ሳይጠፋ ዛሬም ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉን የሚገልጹት አቶ ኢብራሂም፤ አቅጣጫውን በመቀየር ወደ ሳቡሬ እና ወደ ዶሆ አቅጣጫ ወዳለው የተራራው ክፍል መዛመቱን አመልክተዋል።
ሆኖም በተራራው ላይ የተከሰተው እሳት አሁንም ድረስ “ከመተሐራ ከተማ አካባቢ ይታያል” ሲሉ አክለዋል። በፈንታሌ ተራራ ላይ የሰደድ እሳት ሲከሰት የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳልሆነ የሚያስታውሱት አቶ ኢብራሂም፤ “ልጆች እያለን በተደጋጋሚ ሲከሰት እናውቃለን” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በፈንታሌ ተራራ የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ “ወደ ተራራው አናት እንደወጣ” የጠቆሙት የአዋሽ ፈንቲዓሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደን፤ “በወረዳው ህዝብ ላይ ጉዳት ሊያስከትል የማይችል መሆኑን” ገልጸዋል። “ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን” ለወረዳው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያስታወቁት አቶ አደን፤ የአዋሽ ፈንቲዓሌ ወረዳ ነዋሪ “ያለ አንዳች ስጋት የእለት ከእለት ስራውን በተረጋጋ መንፈስ እንዲሰራ” አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























