የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በሚወዛገቡበት የወልቃይት አካባቢ የሚኖረው ህዝብ፤ “በተገቢው ጊዜ” “የፖለቲካ እጣ ፈንታውን እንዲወስን” ሊደረግ እንደሚገባ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ አሳሰቡ። የአካባቢዎች ነዋሪዎችን የወደፊት የኑሮ ሁኔታ በተመለከተ፤ አሜሪካ “በኢትዮጵያ የሚመራ” እና “በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እገዛ የሚደረግለትን” ሂደት እንደምትደግፍም ገልጸዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ ይህን ያሉት፤ ዛሬ ሐሙስ ጥር 7፤ 2018 ዓ.ም በሁመራ ያደረጉትን ጉብኝት በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት ነው። ማሲንጋ በዚሁ መልዕክታቸው በሁመራ በነበራቸው ቆይታ፤ በአካባቢው ያለው ህዝብ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በአይናቸው መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው ባሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱን፣ የሕክምና አገልግሎቶች የተገደቡ መሆናቸውን እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች እጥረት መኖሩን አምባሳደሩ በመልዕክታቸው ዘርዝረዋል። እነዚህ ተግዳሮቶች በብዙዎች ሕይወት ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ መቀጠሉን የገለጹት ማሲንጋ፤ እነዚህን ችግሮች በአስቸኳይ እንዲስተካከሉ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ፍላጎት ጠቁመዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ላይ ለዓመታት ጥገኛ ሆነው እንደሚገኙ ያስታወሱት የአሜሪካው አምባሳደር፤ “ሰብአዊ እርዳታ ወሳኝ ቢሆንም፣ የረጅም ጊዜ መፍትሔ ግን አይደለም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። እያንዳንዱ ግለሰብ በሰላም እና በክብር ህይወቱን ዳግም የት መመስረት እንዳለበት እንዲወስን የሚያስችለውን ሂደት ሀገራቸው እንደምትደግፍም ማሲንጋ አስታውቀዋል።
ይህ ሂደት “በኢትዮጵያ የሚመራ” እና “በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እገዛ የሚደረገለት” እንደሆነም በመልዕክታቸው ጠቁመዋል። ወደፊት ሊያስኬድ የሚችለው መንገድ “ውስብስብ” እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ማሲንጋ፤ ይህም ቢሆን ግን ቅድሚያ መሰጠት ያለበት በአካባቢው ባለው ሁኔታ “በእጅጉ የተጠቁ” ሰዎች “ደህንነት” እንደሆነ አመልክተዋል።
ሁሉም ወገኖች “ከፖለቲካ በላይ ህዝቡን እንዲያስቀድሙ” በመልዕክታቸው የጠየቁት የአሜሪካው አምባሳደር፤ በአካባቢው ያለው ህዝብ “በተገቢው ጊዜ” “የፖለቲካ እጣ ፈንታውን እንዲወስን” ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት፤ አሜሪካ በቁርጠኛኝነት መደገፏን እንደምትቀጥልም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ በአማራ ክልል ስር እየተዳደረ ወደሚገኘው አወዛጋቢ አካባቢ የተጓዙት፤ ከቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ነው። የዛሬውን ጉብኝት በፌስቡክ ገጹ አስቀድሞ ይፋ ያደረገው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን፤ የአሜሪካው አምባሳደር፣ ወደ ስፍራው አብሯቸው የተጓዘው የልዑካን ቡድናቸው እና አቶ ጌታቸው አቀባበል ሲደረግላቸው በፎቶ አስደግፎ አሳይቷል።

ለአሜሪካው አምባሳደር አቀባበል ያደረጉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳደሪ አቶ አሸተ ደምለው ናቸው። የአማራ ክልል “ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን” ብሎ የሚጠራው ይህ አካባቢ፤ በትግራይ “ምዕራብ ትግራይ ዞን” በመባል የሚታወቅ እና ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፊት በትግራይ ክልል ስር ይተዳደር የነበረ ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ፤ “አወዛጋቢ ቦታዎች” በተመለከተ ያሉ ጉዳዮች የሚፈቱት በኢፌዲሪ ህገ መንግስት መሰረት እንደሆነ ሰፍሯል። የፕሪቶሪያው ስምምነት አንዱ ፈራሚ የሆነው የፌዴራል መንግሥት፤ የወልቃይት እና ሌሎች አወዛጋቢ ቦታዎችን ጉዳይ “በሕዝበ-ውሳኔ” ለመፍታት የሚያስችሉ ሂደቶችን እንደሚተገብር በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ በትግራይ ክልል ባለሥልጣናት በተለይም በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተቀባይነት አላገኘም። የወልቃይት አካባቢ “በትግራይ ክልል ስር መሆን አለበት” የሚል አቋም የሚያራምደው ህወሓት፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው ከመመለሳቸው በፊት የምዕራብ ትግራይ ዞን አካባቢውን ማስተዳደር እንዳለበት ይሟገታል።
የአካባቢው አስተዳደር ጉዳይ በሕዝበ-ውሳኔ መፍትሔ ማግኘት እንዳለበት የሚገልጸው የፌዴራሉ መንግሥት በበኩሉ፤ ህወሓት “ተፈናቃዮችን መያዣ ማድረጉን” በመግለጽ ይከሳል። በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮቹ ወደ ቀደመ መኖሪያቸው እንዲመለሱ የሚያስችል ሁኔታ እንዳለም ይገልጻል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]





























