ለአዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ 45 የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያዎች ተጨማሪ የሆነ ጣቢያ ግንባታ ከትላንት በስቲያ መጀመሩን የከተማይቱ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አስታወቀ። ጣቢያው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያሉትን የካ፣ ቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
አዲሱ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የሚገነባበት ስፍራ፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 “ጎሮ” በሚባለው አካባቢ የሚገኝ ነው። “ሲጂሲ ኦሲ” በተባለው ስራ ተቋራጭ ኩባንያ የሚገነባው ይህ ጣቢያ፤ በቀን 52 ሺህ ሜትር ኪዩብ ወይም 52 ሚሊዮን ሊትር ፍሳሽ ቆሻሻን የማጣራት አቅም ይኖረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ መገንባት ካስፈለገባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ማጣሪያዎች በቂ ባለመሆናቸው ምክንያት እንደሆነ የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰርካለም ጌታቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ለዚህም ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከጎሮው የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ በተጨማሪ በቦሌ ክፍለ ከተማ “ኪቲሜ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሌላ ጣቢያ እያስገነባ ይገኛል።

የኪቲሜው ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት 37 በመቶ መድረሱን የጠቆሙት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ፤ ስራ ሲጀምር በቀን 54 ሺህ ሜትር ኪዩብ ወይም 54 ሚሊዮን ሊትር ፍሳሽ ቆሻሻ የማጣራት አቅም ያለው እንደሚሆን ገልጸዋል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ስራ ያስገባው በቦሌ አራብሳ አካባቢ ያስገነባው ሌላ ማጣሪያ፤ በቀን 30 ሚሊዮን ሊትር ፍሳሽ ቆሻሻ በማጣራት ላይ እንደሚገኝም አክለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ካሉ የፍሳሽ ማጣሪያዎች ውስጥ በአቅሙ ትልቁ የሆነው ጣቢያ የሚገኘው በቃሊቲ ነው። በቀን 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ ቆሻሻ ወይም ከ100 ሚሊዮን ሊትር በላይ ፍሳሽ ቆሻሻ የማጣራት አቅም ያለው ይህ ጣቢያ፤ ስራ የጀመረው በ2010 ዓ.ም ነበር። ከሁለት ቢሊዮን በላይ ብር በሆነ ወጪ ያስወጣው የቃሊቲው ማጣሪያ፤ ለ1.5 ሚሊዮን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ እንደሆነ ከባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በምስራቅ አዲስ አበባ ተፋሰስ ስር ያሉት የጎሮ እና የኪቲሜ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያዎች፤ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ በየዕለቱ በድምሩ 106 ሺህ ሜትር ኪዩብ ወይም 106 ሚሊዮን ሊትር ፍሳሽ ቆሻሻ የማጣራት አቅም ይኖራቸዋል። የሁለቱ ማጣሪያ ጣቢያዎች ግንባታ፤ ከመኖሪያ ቤቶች እና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚለቀቁ ፍሳሽ ቆሻሻዎች የሚወገዱባቸው መስመሮች ዝርጋታን የሚያካትት ነው።

ከትላንት በስቲያ ግንባታው የተጀመረው የጎሮ ማጣሪያ ጣቢያ፤ የ205 ኪሎ ሜትር ቀላል እና ከባድ የፍሳሽ ቆሻሻ ማሰባሰቢያ መስመር እንደሚዘረጋለት የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። አዲሱ ማጣሪያ ጣቢያ ካስፈለገባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ የከተማይቱ ነዋሪዎች “የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽን ወደ ወንዞች እንዳይለቁ” የሚከለክል ህግ መውጣቱን ተከትሎ የፍሳሽ ቆሻሻ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ፤ “የቆሻሻ አወጋገድን ዘመናዊ ማድረግ በማስፈለጉ” ምክንያት እንደሆነ የባለሥልጣኑ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አስረድተዋል።
በፌደራል ደረጃ የተዘጋጀው “የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ” በፓርላማ የጸደቀው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ነበር። ይህ አዋጅ ከመውጣቱ አምስት ወር አስቀድሞ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የወንዞን ብክለት ለመከላከል የሚያስችል ደንብ አጽድቋል።
በታህሳስ 2017 ዓ.ም የጸደቀው ይህ ደንብ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ወንዞችን በባህሪያቸው “አደገኛነት” ባላቸው ደረቅም ይሁን ፈሳሽ ቆሻሻ በሚበክሉ ድርጅቶች ላይ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ቅጣት የሚጥል ነው። ከመኖሪያ ቤቶች የሽንት ቤት አሊያም ማንኛውንም ያልተጣራ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ መልቀቅ ደግሞ በደንቡ መሰረት እስከ 300 ሺህ ብር ያስቀጣል።

የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፤ ከኢንዱስትሪዎች ወይም ፋብሪካዎች ከሚለቀቁ የፍሳሽ ተረፈ ምርቶች እና ከጎርፍ ፍሳሾች በስተቀር “ከመኖሪያ ቤቶች እና ከተቋማት የሚለቀቁ ፍሳሾችን” በተለያዩ መንገዶች የማስወገድ ሥራ ያከናውናል። ፍሳሾችን በተሽከርካሪዎች እና በማስተላለፊያ መስመሮች አማካኝነት ወደ ማጣሪያ ቦታዎች በማጓጓዝ እንዲጣሩ ማድረግ ባለሥልጣኑ ከሚያከናውናቸው ስራዎች መካከል ይጠቀሳል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቦታዎች ባሉ ማዕከላት የፍሳሽ ማጣራት ሥራዎች የሚከናወኑት፤ ከከተማይቱ ነዋሪዎች እና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚለቀቁ ፍሳሾች “የሰው ልጆች ጤናን እና ከባቢን እንዳይበክሉ” ለማድረግ እንደሆነ የባለሥልጣኑ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ይገልጻሉ። ይህን ተግባር እንዲያከናውን ግንባታው የተጀመረው የጎሮ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ በግንቦት 2019 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የጎሮ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ የሚከናወነው ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር ነው። የዓለም ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄዱ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ማዕከላትን እና ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት፤ በሁለት ዙር የሚለቀቅ የብድር ፕሮግራሞችን የፈቀደው በመጋቢት 2009 ዓ.ም ነበር።

ባንኩ ለዚሁ ፕሮግራም በ2009 ዓ.ም. 445 ሚሊዮን ዶላር ብድር ያጸደቀ ሲሆን ለሁለተኛው ዙር የሚውል 275 ሚሊዮን ዶላር ብድርንም በተመሳሳይ መልኩ በ2016 ዓ.ም. አጽድቋል። ይህ ብድር 3.2 ሚሊዮን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን “በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ” የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገድ ስራዎችን ጨምሮ የንጹህ መጠጥ ውሃ አሰራሮችን ለማዘመን የሚውል እንደሆነ የዓለም ባንክ በግንቦት 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























