በስፖርታዊ ዝግጅቶች ላይ “ማንኛውንም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን” ማካሄድ የሚያግድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ሊቀርብ ነው

በዜጎች “ደህንነት”፣ “ሰላም” እና “ጤና” ላይ “ከፍተኛ ተጽዕኖ” የሚያስከትል አደጋ “እንደሚከሰት ሲታመን”፤ ማንኛውም የስፖርት ኩነት እንዳይካሄድ ለማገድ የሚያስችል የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። ስፖርታዊ ዝግጅቶች ከመጀመራቸው በፊትም ሆነ በሚካሄዱበት ወቅት “ማንኛውንም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን” ማካሄድ እንደማይቻልም የአዋጅ ረቂቁ ይከለክላል።

“የፌደራል የስፖርት ልማት እና አስተዳደር አዋጅ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የአዋጅ ረቂቅ፤ ነገ ሐሙስ ጥር 14፤ 2018 በሚካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ እንዲቀርብ አጀንዳ ተይዞለታል። በዚህ የአዋጅ ረቂቅ ላይ የተወያየው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ ግብአቶችን በማከል ወደ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ የወሰነው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።

አዋጁ የተዘጋጀው የስፖርት ዘርፉ የሚመራበትን እና የሚተዳደርበትን “ወጥ”፣ “ፍትሃዊ” እና “ግልጽ” “የአሰራር ስርዓት” መዘርጋት በማስፈለጉ እንደሆነ በረቂቅ የህግ ሰነዱ መግቢያ ላይ ሰፍሯል። በ70 አንቀጾች የተከፋፈለው ይህ አዋጅ በውስጡ ከያዛቸው ክፍሎች ውስጥ የስፖርት ተቋማትን ስለማቋቋም እና ስለማስተዳደር፣ የስፖርት ፋይናንስ አስተዳደር እንዲሁም የስፖርት ግጭት አፈታት ስርዓትን የተመለከቱት ይገኙበታል።

የስፖርት ኩነቶች አስተዳደር እና የሽልማት አሰጣጥ ስርዓትን የተመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎችም በአዋጁ ረቂቁ ተካትተዋል። የስፖርት ኩነት “ስፖርታዊ እንቅስቃሴ፣ መዝናኛ ፣ ፌስቲቫል፣ ስብሰባ፣ ሴሚናር፣ ሲምፖዚየም፣ ኮንፈረንስ እና ወርክሾፕን” እንደሚያጠቃልል  በአዋጁ የትርጓሜ ክፍል ላይ ሰፍሯል።

ሀገር አቀፍ የስፖርታዊ ኩነቶች ተብለው በአዋጅ ረቂቁ ከተዘረዘሩት መካከል የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ፣ ሀገር አቀፍ የክለቦች ሻምፒዮና፣ ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ስፖርት ፌስቲቫል፣ የመከላከያ ወይም የፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል ይገኙበታል። በአዋጁ ላይ ከሰፈሩት በተጨማሪ “ማንኛውም የፌደራል ስፖርት ማህበር ሌሎች ስፖርታዊ ኩነቶችን በመቅረጽ ሊተገብር እንደሚችልም” ረቂቅ የህግ ሰነዱ ይፈቅዳል።

የአዋጅ ረቂቁ “የስፖርት ኩነቶችን ማገድ” የሚቻልበትን ድንጋጌም በውስጡ አካትቷል። የስፖርት ኩነቶች ሊታገድ የሚችለው “በዜጎች ደህንነት፣ ሰላም እና ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያስከትል ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ወይም እንደሚከሰት ሲታመን” እንደሆነ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። 

የስፖርት እና ባህል ሚኒስቴር እገዳውን የሚጥለው “ከመንግስት አካል ሪፖርት ሲደርሰው” መሆኑም በአዋጁ ረቂቁ ላይ ተመልክቷል። ሆኖም ረቂቅ ህጉ “የመንግስት አካል” የተባለው የትኛው ተቋም ወይም መስሪያ ቤት እንደሆነ በግልጽ አላሳወቀም።

ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የስፖርት ኩነቶችን በዋነኛነት ሲያስተናግድ በቆየው በአዲስ አበባ ስታዲየም ሊካሄዱ የነበሩ ውድድሮች፤ “በጸጥታ ስጋት” እና በሌሎችም ምክንያቶች “ሲሰረዙ” እና “ላልተወሰነ ጊዜ” ሲተላለፉ ቆይተዋል። ለዓመታት በእድሳት ላይ የቆየው የአዲስ አበባ ስታዲየም፤ ባለፈው ሰኔ ወር ጨዋታ ለማስተናገድ ሲከፈት ተመሳሳይ ችግር ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል።  

ስታዲየሙ በወላይታ ድቻ እና በሲዳማ ቡና መካከል የሚደረገውን የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜን እንደሚያስተናግድ ከሳምንታት በፊት ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፤ በዋዜማው በተላለፈ ድንገተኛ ውሳኔ ጨዋታው ያለ ተመልካች እንዲከናወን ተደርጓል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታው “በዝግ እንዲከናወን” ውሳኔ ያሳለፈው፤ “ከአቅም በላይ በሆነ” ምክንያት እንደሆነ በወቅቱ ገልጾ ነበር።

በዚህ ውሳኔ የተቆጡ እና ተቃውሟቸውን የገለጹ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ለቀናት በአዲስ አበባ ታስረው መቆየታቸው የሚታወስ ነው። የፌደራል ፖሊስ “ግጭት ለማባባስ ሲንቀሳቀሱ ነበር” በማለት በቁጥጥር ስር ካዋላቸው የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች መካከል ከሀዋሳ፣ ከወላይታ ሶዶ እና ከአካባቢው የመጡ ይገኙበታል።

ነገ ለፓርላማ የሚቀርበው የአዋጅ ረቂቅ “በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ውስጥ ሁከት ሊያስነሳ የሚችል ድርጊት መፈጸምን” ይከለክላል። በእነዚህ ስፍራዎች ውስጥ “ማናቸውንም አይነት በቃል፣ በዜማ፣ በጽሑፍ፣ በምልክት እና በአለባበስ የሚገለጹ”፤ “መልካም ስነ ምግባርን የሚጻረሩ” እና “ሁከትን ሊያነሳሱ የሚችሉ” ድርጊቶችን መፈጸም የተከለከለ መሆኑን አዋጁ ደንግጓል።  

የህግ ረቂቁ “የዘረኝነት እና የማህበራዊ ልዩነትን የሚያንጸባርቁ” ያላቸውን “ማናቸውንም ዓይነት ድርጊቶች” መፈጸም ላይም በተመሳሳይ ሁኔታ ክልክላ ጥሏል። “ማናቸውንም አይነት የፖለቲካ ወይም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች” ስፖርታዊ ዝግጅቶች “ከመጀመራቸው በፊት” አሊያም “በሚካሄዱበት ወቅት” ማካሄድ እንደማይቻልም በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

ይህን ድንጋጌ በመተላለፍ ጥፋት የፈጸመ ሰው “እንደነገሩ አግባብነት” እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት እና እስከ ሃምሳ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ በህግ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል። በአዋጅ ረቂቁ የተከለከለው ሌላው ተግባር “በሰው ጤና፣ አካል ወይም ስነ-ልቦና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ስለታማ መሳሪያዎችን” ወደ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ይዞ መግባት ነው።

ወደ እነዚህ ስፍራዎች “የተለያዩ የሚተኮሱ፣ የሚወረወሩ፣ የሚፈነዱ፣ የሚቀጣጠሉ ወይም መርዛማ ቁሳቁሶችን” ይዞ መግባትም እንደዚሁ በተመሳሳይ ክልክል መሆኑ በአዋጅ ረቂቁ ተመልክቷል። ይህንን በመተላለፍ ወንጀል የፈጸመ ማንኛውም ሰው፤ “እንደነገሩ ሁኔታ” እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ቅጣት እንደሚጣልበት የአዋጅ ረቂቁ ደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)