የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ፍላጎት ከአቅርቦት በ24 ሚሊዮን ዶላር በለጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባካሄደው የውጭ ምንዛሬ ጨረታ፤ የባንኮች ፍላጎት ከአቅርቦት በ24.7 ሚሊዮን ዶላር በለጠ። ብሔራዊ ባንክ በዛሬው ዕለት ባካሄደው የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ከተሳተፉ 21 ባንኮች መካከል ስድስቱ ዶላር ሳያገኙ ቀርተዋል።

ብሔራዊ ባንክ በየሁለት ሳምንት ልዩነት “መደበኛ እና “ተከታታይ” የውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ጨረታ ማካሄድ የጀመረው ከመጋቢት 2017 ዓ.ም መጨረሻ አንስቶ ነው። በዚህም መሰረት ባንኩ 15ኛውን ዙር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ፤ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 12፤ 2018 አካሄዷል።

በዚሁ ጨረታ ማዕከላዊው ባንክ ለጨረታ ያቀረበው 70 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፤ በጨረታው የተሳተፉ ባንኮች ባቀረቡት ዋጋ የተጠየቀው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሬ መጠን ግን 94.7 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረገው የውጤት መግለጫ ያሳያል። ይህ የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት፤ ብሔራዊ ባንክ ካቀረበው የገንዘብ መጠን በ24.7 ሚሊዮን ዶላር የላቀ ነው።

በዛሬው ጨረታ ለአንድ ዶላር የቀረበው ከፍተኛ ተመን 155 ብር ሲሆን ዝቅተኛው 153 ብር ነበር። አንድ ዶላር በጨረታው የተመነዘረበት አማካኝ ጭማቂ ዋጋ 154 ብር ከ9207 ሳንቲም ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ 154 ብር ከ78 ሳንቲም  እንደሆነ በብሔራዊ ባንክ መግለጫ ተመልክቷል። 

ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሬ ጨረታዎች ካካሔደ በኋላ አማካኝ ጭማቂ ዋጋ እና የተሳታፊ ባንኮችን ቁጥር ብቻ ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል። ጨረታዎቹን በቅርበት የሚከታተሉ የባንክ እና የፋይናንስ ባለሙያዎች፤ ማዕከላዊው ባንክ ውጤቶችን ይፋ ሲያደርግ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎች እንዲያቀርብ ሲወተውቱ ቆይተዋል። 

ባንኩ በዛሬው የጨረታ ውጤት ተጨማሪ መረጃዎችን ማካተቱ፤ “የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን ለማረጋጋት ያግዛል” ከሚል ዕሳቤ የመነጨ ሊሆን እንደሚችል አንድ የፋይናንስ ባለሙያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ባለፈው ሳምንት በተካሔደው የ“ፋይናንስ እመርታ” በተሰኘ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ገለጻ፤ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ለውጥ ከመደረጉ በፊት 100 ፐርሰንት አካባቢ የነበረው የትይዩ ገበያ እና የመደበኛ ገበያ የምንዛሬ ልዩነት ወደ 13 ፐርሰንት አካባቢ ዝቅ ማለቱን አስታውቀው ነበር።

ብሔራዊ ባንክ እና የገንዘብ ሚኒስቴር፤ ኢትዮጵያ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ ያዋለችው የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ማሻሻያ ስኬታማ እንደሆነ ያምናሉ። ወደ ግልጽ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ የተደረገ ሽግግር እና በገበያ ላይ ወደ ተመሰረተ ስርዓት ለመሻገር የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ ከሆኑ የማሻሻያው ተግባራት መካከል እንደሆኑም ይጠቅሳሉ።  

ሁለቱ ተቋማት በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያን አስመልክቶ ያካሄዱትን አራተኛ የጋራ ግምገማ ተከትሎ በዛሬው ዕለት ባወጡት መግለጫ፤ በውጭ ምንዛሬ ስርዓት ላይ የተደረገው ማሻሻያ “ተዓማኒነትን መመለስ፣ የሸቀጦች የወጪ ንግድን ተወዳዳሪነት ማሻሻል እና የግሉን ዘርፍ እንቅስቃሴዎች መደገፍ” እንደቻለ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)