የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የግብጹን ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲን ማገናኘት እንደሚፈልጉ ተናገሩ። ትራምፕ ሁለቱን መሪዎች ማገናኘት የሚፈልጉት፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ የሚፈታ ስምምነት ለማበጀት እንደሆነ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት፤ በስዊትዘርላንድ ዳቮስ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ከግብጹ አቻቸው ጋር ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ነው። ዛሬ ረቡዕ ምሽት በተካሄደው በሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ውይይት ላይ፤ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የግብጽ አቻቸው ባድር አብደላቲን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ትራምፕ ውይይቱን ሲጀመሩ “ከግብጽ ጋር በጣም ጥሩ ግንኙነት አለን። ፕሬዝዳንቱ ደውለው አንዳች ነገር ይጠይቃሉ። ሁል ጊዜም መፍትሔ እናገኝለታለን” ሲሉ ተደምጠዋል። አልሲሲ በፊናቸው ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ ወዲህ “በስኬቶች የተሞላ ዓመት” እንዳሳለፉ ጠቅሰው አሞግሰዋቸዋል።

የግብጹ ፕሬዝደንት በአረብኛ ቋንቋ ባሰሙት ንግግር እርሳቸው ባሉበት የዓለም ክፍል “እጅግ ከባድ” ያሉትን የጋዛ ጉዳይ አንስተዋል። በዚህ ጉዳይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስመዝግበውታል ላሉት ስኬትም “እንኳን ደስ አለዎ” ብለዋቸዋል። ዶናልድ ትራምፕ ባይሆኑ ኖሮ “በጋዛ ከስምምነት አይደረስም ነበር” ያሉት አልሲሲ፤ ለጉዳዩ “ትኩረት” መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ሲደረግ የነበረው ውጊያ በተኩስ አቁም ስምምነት ከቆመ ወዲህ፤ ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ የግብጽ ፕሬዝዳንት በዚሁ ንግግራቸው አሳስበዋል። ሁለተኛው ምዕራፍ “ስኬታማ እንዲሆን በእኛ በኩል የምንችለውን ሁሉ ለማቅረብ ዝግጁ ነን” ሲሉም ቃል ገብተዋል።
አልሲሲ የስምምነቱን አተገባበር እና የጋዛን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በበላይነት ለመምራት ትራምፕ እያቋቋሙት በሚገኘው “የሰላም ቦርድ” አባል እንዲሆኑ በመጋበዛቸው ደስታቸውን ገልጸዋል። “የሰላም ቦርድ አባል በመሆናችን ደስተኛ ነን። በእኛ የዓለም ክፍል እና በዓለም ዙሪያ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን እያንዳንዱን ጥረት እንደግፋለን” ሲሉ አልሲሲ በአስተርጓሚያቸው በኩል ለትራምፕ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም አሳውቀዋል።

የግብጹ ፕሬዝዳንት “የህልውና ጉዳይ” ያሉትን የናይል ወንዝን እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ትራምፕ ለሀገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አመስግነዋል። በትራምፕ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን በግድቡ ጉዳይ ላይ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት አልሲሲ፤ በወቅቱ ተዘጋጅቶ የነበረው ስምምነት እንዲፈረም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት “ሁሉንም ነገር” ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕም በምላሻቸው የታላቁ ህዳሴን ግድብ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው ተናግረዋል። ትራምፕ በዚሁ ንግግራቸው የህዳሴውን ግድብ ከዓለም ግዙፍ ግድቦች አንዱ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የግንባታ ወጪውን የሸፈነችው ሀገራቸው እንደሆነች ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ የህዳሴውን ግድብ ወጪ በአሜሪካ መሸፈኑን በተመለከተ ሲናገሩ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫም ይህንኑ አስተጋብተው ነበር። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የወጪውን ጉዳይ የተመለከተ አወዛጋቢ አስተያየት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰጡት በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ወቅት ነው።

ትራምፕ በዛሬው ንግግራቸው ላይም በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ላይ እጃቸውን ያስገቡት በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው መገባደጃ እንደሆነ አስታውሰዋል። “ለስምምነት ተቃርበን ነበር። ይሁንና በተጭበረበረ ምርጫ ሥልጣን ለቀቅኩ” በማለት በእርሳቸው አረዳድ ድርድሩ ሳይቋጭ የቀረበትን ምክንያት አስረድተዋል።
ትራምፕ ወደ ሥልጣን ሲመለሱ “ግድቡ በጣም አደገኛ ጉዳይ” ሆኖ እንዳገኙት ገልጸው፤ “ወደነበረበት መመለስ እችል እንደሆነ አያለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል። “ግድቡ የናይል ወንዝን ይገታል” ያሉት ትራምፕ፤ “ከረዥም ጊዜ በፊት ሲገነቡት እና ፋይናንስ ሲያደርጉት ውይይት ሊደረግበት የሚገባ ነበር” ሲሉ የግብጽን አቋም ያስተጋባ የመሰለ አስተያየት ሰጥተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በዛሬው ንግግራቸው፤ በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረት ለፈጠረው ልዩነት መፍትሔ ለማበጀት “የተለያዩ የጋራ ሙከራዎች” እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። የ79 ዓመቱ የአሜሪካ መሪ የሙከራዎቹን ምንነት በዝርዝር ሳያብራሩ ቢቀሩም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ፕሬዝዳንት አልሲሲን ፊት ለፊት የማገናኘት ሃሳብ እንዳላቸው ግን አሳውቀዋል።

ትራምፕ ላለፉት 12 ገደማ ዓመታት ግብጽን በመምራት ላይ የሚገኙትን አብደል ፋታህ አልሲሲን “ጠንካራ መሪ” ሲሉ ጠርተዋቸዋል። “በኢትዮጵያ ጠንካራ መሪ እንዳለ ሰምቼያለሁ” ያሉት ትራምፕ፤ ይሁንና “አንተን እንደማውቀው እሱን አላውቀውም። ነገር ግን ጠንካራ ሰው ነው። ስምምነት ማድረግ እንችል እንደሆነ ለማየት ሁለታችሁን ለማገናኘት እሞክራለሁ” ሲሉ ለግብጹ ፕሬዝዳንት ነግረዋቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























