ኢትዮጵያ ከቻይና እና ከብራዚል ጋር ፍርደኞችን ለማስተላለፍ ያደረገችው የስምምነት አዋጅ በፓርላማ ጸደቀ። ስምምነቱ በተለያዩ ወንጀሎች ምክንያት የተፈረደባቸው የየሀገራቱ ዜጎች፤ ፍርዳቸውን በሀገራቸው እንዲፈጽሙ የሚያስችል ነው።
ከሁለቱ ሀገራት መንግሥታት ጋር በተደረገ ስምምነት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀው አዋጅ የጸደቀው፤ ዛሬ ሐሙስ ጥር 14፤ 2018 በተካሄደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። ለዛሬው መደበኛ ስብሰባ ከተያዙ ዘጠኝ አጀንዳዎች መካከል አምስቱ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር የተፈራረመቻቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶችን የተመለከቱ ነበሩ።
በአዋጅ መልክ ከተዘጋጁት ከእነዚህ ስምምነቶች መካከል በአራቱ ላይ የተዘጋጀውን ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ፤ በተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ አቅርበዋል። ከስምምነቶቹ አንዱ የሆነው በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ፍርደኞችን ማስተላለፍን የሚፈቅደው አዋጅ፤ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች የሚገኙ ቻይናውያን ፍርደኞች ወደ ሀገራቸው እንዲዛወሩ እንደሚያስችል የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገልጸዋል።
አዋጁ በተመሳሳይ በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፍርደኞችም ወደ ሀገራቸው መዛወር እንዲችሉ የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል። በተለያዩ ወንጀሎች ምክንያት የተፈረደባቸው ዜጎች፤ ፍርዳቸውን በሀገራቸው ውስጥ ከሚያውቁት ማህበረሰብ፣ ቋንቋ እና ባህል ጋር በቅርበት ሆነው እንዲፈጽሙ እና ታርመው ወደ ማህበረሰባቸው እንዲቀላቀሉ የሚያስችል አዋጅ መሆኑንም እጸገነት አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል የተደረሰው ስምምነት፤ ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረገ እና ውጤታማ የሆነ የፍርደኞችን ሰብዓዊ መብት የጠበቀ ትብብር ማድረግ የሚያስችል መሆኑን የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ አስረድተዋል። በአዋጁ ላይ ጥያቄ ከሰነዘሩ ሁለት የፓርላማ አባላት አንዱ የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፤ ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት እኩል ተፈጻሚ መሆኑን በተመለከተ ጥያቄ አንስተዋል።
ዓለም በአሁኑ ሰዓት “በህግ ሳይሆን በኃይል እየተመራች” መሆኗን የጠቀሱት የግል የፓርላማ ተመራጩ ኡስታዝ ካሚል፤ በቻይና እና በኢትዮጵያ መካከል ካለው የኃይል ሚዛን ልዩነት አንጻር “እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል። አዋጁ “ከዲፕሎማሲ የዘለለ ፋይዳ አለው ወይ? የህግ ተፈጻሚነቱስ ምን ያህል ነው?” ሲሉም ተከታይ ጥያቄ ሰንዘረዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተመራጩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ እንደዚህ አይነት የሁለትዮሽ ስምምነቶች “የሀገሪቱን ብሔራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ይጎዳል” የሚል ግምገማ እንዳላቸው ለምክር ቤቱ ገልጸዋል። ቻይናውያን ዜጎች “በተለይ እና በተደጋጋሚ” የሚሳተፉባቸው በሚዲያ የሚሰሙ “የታወቁ ወንጀሎች” መኖራቸውን ያነሱት የፓርላማ አባሉ፤ ወንጀሎቹ በከፍተኛ ሁኔታ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ጥቅም የሚጎዱ እንደሆኑ አስረድተዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ ቻይናውያን “ጎላ ብለው የሚታዩባቸው” በማለት የጠቀሷቸው ወንጀሎች “ህገወጥ የማዕድን ማውጣት እና ማዘወዋር” እንዲሁም “በህገ ወጥ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ” (money laundering) ናቸው። በእንደዚህ አይነት ወንጀሎች የሚሳተፉ ዜጎች በኢትዮጵያ የህግ ስነ ስርዓት “እዚሁ የፍርድ ሂደታቸውን ማጠናቀቅ አለባቸው” ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት የፓርላማ አባሉ፤ ግለሰቦቹ ተፈርዶባቸው ወደ ሀገራቸው ከተላለፉ በኋላ “ፍርዱ እዚያ ስለመፈጸሙ ምን ቁጥጥር አለን?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እጸገነት፤ አዋጁ “ፍርደኞች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ይለቀቃሉ” የሚል አንደምታ እንደሌለው አንስተዋል። ፍርደኞችን ለመለዋወጥ ሕጋዊ ስምምነት ያስፈለገው “ለአሰራር ምቾት” በማሰብ እንጂ አስቀድሞም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እስረኞችን የማስተላለፍ ስራ ሲከናወን እንደነበረ አስታውሰዋል።

ከቻይና ተመልሰው በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፍርደኞች መኖራቸውን የቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የመስክ ምልከታ ማረጋገጡን ሰብሳቢዋ ለዚህ በማሳያነት አንስተዋል። ፍርደኞቹ ከማረሚያ ቤት ሊወጡ የሚችሉት የቻይና መንግሥት ይቅርታ ሲያደርግላቸው መሆኑን እጸገነት ገልጸዋል።
ዛሬ በፓርላማ በጸደቀው የስምምነት አዋጅ መሰረት፤ “በአደንዛዥ እጽ ዝውውር” ተጠርጥራ በቻይና ጉዋንዡ ታስራ የምትገኘው ኢትዮጵያዊት ፍርደኛ ናዝራዊት አበራ ወደ ሀገሯ የመመለስ እድል እንደሚኖራት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አመልክተዋል። ናዝራዊት “አደንዛዥ እጽ ይዛ ተገኝታለች” በሚል በቻይና ቤጂንግ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር የዋለችው በታህሳስ 2011 ዓ.ም ነበር።
የኢንጂነሪንግ ምሩቋ ኢትዮጵያዊት ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። ናዝራዊት እጹን ይዛ የተገኘችው “በጓደኛዋ ተታልላ ነው” መባሉ ለመነጋገሪያነቱ ዋና ምክንያት ነበር። እጽ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሰዎች በቻይና ህግ መሰረት የሞት ቅጣት እንደሚፈረድባቸው መገለጹ፤ በቤተሰቦቿ እና ጉዳዩን ሲከታተሉ በቆዩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል።

በአንድ ተቃውሞ፣ በአብላጫ ድምጽ ዛሬ የጸደቀው አዋጅ ናዝራዊትን ወደ ኢትዮጵያ “ለመመለስ ዕድል ይከፍታል” ያሉት የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ፤ የቻይና ዜጎችም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው “በሚያውቁት ቋንቋ፣ በሀገራቸው፣ በማህበረሰባቸው ውስጥ ፍርዳቸውን እንዲጨርሱ” የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል። አዋጁ ፍርደኞችን “ልቅ ሆነው እንዲለቀቁ የሚያደርግ አይደለም” ሲሉም እጸገነት ተናግረዋል።
ቻይናውያን ዜጎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ይቅርታ ካልተደረገላቸው በስተቀር ፍርዳቸውን ሳይጨርሱ ሊለቀቁ እንደማይችሉም የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህን ሁኔታ መቆጣጠር እና ክትትል ማድረግ በተፈለገ ጊዜ ወደ ቻይና በመሄድ ወይም በኤምባሲ በኩል እስረኞቹን መጎብኘት የሚቻልበት ስርዓት መኖሩን የገለጹት እጸገነት፤ ለቻይና መንግሥትም ይኸው ሂደት በተመሳሳይ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው መደበኛው ስብሰባው፤ በኢትዮጵያ እና በብራዚል መካከልም በተመሳሳይ ፍርደኞችን ማስተላለፍ የሚያስችል አዋጅን አጽድቋል። በኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ መንግሥታት መካከል የተደረገው በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን የአሳልፎ የመስጠት ስምምነት አዋጅም እንዲሁ በዛሬው ስብሰባ ላይ ጸድቋል።

በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርቦ በአንድ ድምጸ ተዐቅቦ፣ በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው ሌላው ስምምነት፤ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል የተደረገ የወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ነው። እነዚህ ስምምነቶች ህዳር 20፤ 2018 በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ በአዋጅ መልክ እንዲጸድቁ “በሙሉ ድምጽ” ለፓርላማ የተመሩ ናቸው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጆቹን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተላለፈው፤ “ስምምነቶቹ ቢጸድቁ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ውጤታማ የወንጀል መከላከል የሁለትዮሽ የህግ ትብብር ማዕቀፍ ለመፍጠር የሚያስችላት መሆኑን በመገንዘብ” እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር የተደረሱት እነዚህ ስምምነቶች፤ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጠናክር የሚያግዙ እንደሆኑ የፓርላማው የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በዛሬው ስብሰባ ላይ አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























