አሜሪካ በህወሓት አመራሮች ላይ የጣለችው የቪዛ እገዳ “በጎደሎ እና ሚዛን ባጣ ግምገማ ላይ የተመሰረተ ነው” ሲል ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተቸ። ሀገሪቱ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ከፈረሙ ወገኖች አንዱን ብቻ መርጣ ተጠያቂ ማድረጓ “በሰላም ሂደት ላይ ያለን እምነት የሚሸረሽር ነው” ሲልም እርምጃውን ተቃውሟል።
የፖለቲካ ፓርቲው ተቃውሞን የገለጸው፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በህወሓት አመራሮች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ በትላንትናው ዕለት የጣለውን የቪዛ እገዳ ተከትሎ በሰጠው ምላሽ ነው። ህወሓት ዛሬ አርብ ሰኔ 12፤ 2018 ምሽት ባወጣው የምላሽ መግለጫ፤ በፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት የተዘረዘሩ ጉዳዮች አለመፈጸማቸውን ጠቅሷል።
ለስምምነቱ አንኳር ነጥቦች አለመፈጸም ህወሓት በመግለጫው ተጠያቂ ያደረገው የፌደራል መንግስትን ነው። ፓርቲው በዛሬው መግለጫው በፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት መሰረት ተግባራዊ ሳይደረጉ ቀርተዋል ካላቸው ጉዳዮች መካከል በቀዳሚነት የተጠቀሰው “የህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ወደነበረበት መመለስ” የሚለው ነጥብ ነው።
ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ ላለመሆኑ ፓርቲው በተጨማሪነት ከጠቀሳቸው ጉዳዮች መካከል የተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው “አለመመለስ” እና ከፌደራል መንግስት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ግዛት “አለመውጣታቸው” ይገኝበታል። የመሰረታዊ አገልግሎቶች እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት “ወደነበረበት አለመመለሱም” ሌላው በህወሓት መግለጫ የተነሳ ጉዳይ ነው።
የህወሓት እውቅና ጉዳይም ሌላው በመግለጫው የተጠቀሰ ነጥብ ነው። ህወሓት “ህጋዊ እና ፖለቲካዊ” እውቅናው “ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት መመለስ አለበት” በሚል በተደጋጋሚ የሚያስተጋባውን አቋሙን በዛሬው መግለጫው ላይም አስፍሯል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በግንቦት 2017 ዓ.ም. ህጋዊ ምዝገባው የተሰረዘው ህወሓት፤ መስሪያ ቤቱ ባለፈው ወር መጨረሻ ባስፈጸመው ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ ላይ የትግራይ ክልል “ተገልሏል” ሲልም በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል። በትግራይ ክልል ለደረሰው ጉዳት “የተጠያቂነት ስርዓት አለመዘርጋቱንም” ህወሓት በመግለጫው በጉድለትነት አንስቶታል።

“የትግራይ ህዝብ ሰላም ይፈልጋል፣ ፍትህ ይገባዋል” ያለው ህወሓት፤ “በእኩልነት፣ በሐቀኝነት እና ሙሉ በሙሉ የሚተገበር የሰላም ሂደት ይገባዋል” ሲል አሳስቧል። አሜሪካ “ለትግራይ ህዝብ መከራ አስተዋጽኦ ያደረጉ ወገኖችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የምትወስዳቸውን እርምጃዎች በፍትሃዊነት እና ወጥ በሆነ መልኩ” ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባትም ህወሓት በመግለጫው አስፍሯል።
የፌደራል መንግስት “በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት የተጣሉበትን ግዴታዎች አላከበረም” ሲል የሚነቅፈው ህወሓት፤ አሜሪካ ይህንን ከመመልከት ራሷን “ገሸሽ አድርጋለች” የሚል አቋም አለው። የፖለቲካ ፓርቲው በመግለጫው “የትግራይ ህዝብ መከራ የህወሓት ግትርነት ውጤት አይደለም” ቢልም፤ አሜሪካ ትላንት ባወጣችው መግለጫ ግን የቪዛ እገዳ የጣለችው “በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ረገድ ተጠያቂ የሆኑትን ወይም ተባባሪ የሆኑ ግለሰቦችን” እንደሆነ አስታውቃለች።
አሜሪካ የጣለችውን የቪዛ እገዳ የተቃወመው ህወሓት በበኩሉ፤ እርምጃው “በሰላም ሂደት ላይ ያለን እምነት የሚሸረሽር ነው” ብሏል። ሀገሪቱ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ከፈረሙ ወገኖችን” አንዱን ብቻ መርጣ ተጠያቂ ማድረጓን” የተችው ህወሓት፤ “ዘላቂ ሰላም ገለልተኝነትን፣ ወጥነትን እና የሁሉም ወገኖች እኩል ተጠያቂነትን ይፈልጋል” ሲልም አቋሙን ገልጿል።

ህወሓት በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ በአሜሪካ በኩል መደረግ አለባቸው ብሎ ከዘረዘራቸው አምስት ጉዳዮች መካከልም ይህንኑ አካትቷል። የፌደራል መንግስት በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት የተጣሉበትን ግዴታዎች “በሙሉ እንዲተገብር” አሜሪካ ግፊት እንድታደርግም ህወሓት ጠይቋል።
አሜሪካ ከቀያቸው የተፈናቀሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች “ደህንነታቸው ተጠብቆ፣ በክብር እና በተወሰነ የጊዜ ገደብ እንዲመለሱ” ድጋፍ እንድታደርግም ህወሓት ጥሪ አቅርቧል። ከፌደራል መንግስት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ግዛት እንዲወጡ አሜሪካ እንድትሟገትም የፖለቲካ ፓርቲው በተመሳሳይ ጥሪውን አስተላልፏል።
ህወሓት ሌላው በጥሪው ያካተተው፤ የፖለቲካ ፓርቲውን ህልውና ወደነበረበት የመመለስ ጉዳይ ነው። በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የህወሓት “ህጋዊ እና ፖለቲካዊ ህልውና እንዲመለስ” አሜሪካ ድጋፍ እንድታደርግ ህወሓት በዛሬው መግለጫው በይፋ ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]






























