በትግራይ የሚደረጉ የሰላም ጥረቶችን “የሚያደናቅፉ” ላለቻቸው አካላት አሜሪካ ማሳሰቢያ ሰጠች   

የአሜሪካ ኤምባሲ በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት እየተካሄዱ ያሉ የሰላም ሂደቶችን “የሚያደናቅፉ” አካላት፤ በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው የውይይት ጥረት “በአስቸኳይ ትብብር” እንዲያደርጉ አሳሰበ። የፖለቲካ መሪዎች የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነትን “ሙሉ ለሙሉ” ተግባራዊ ማድረጋቸው “እጅግ አስፈላጊ” መሆኑንም ኤምባሲው ገልጿል።

ኤምባሲው ይህን የገለጸው፤ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ በቃል አቃባዩ በኩል ዛሬ አርብ ሰኔ 19፤ 2018 ባወጣው መግለጫ ነው። የዛሬው መግለጫ፤ አሜሪካ “አክራሪ” ባለቻቸው የህወሓት አባላት እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ገደብ መጣሏን ካሳወቀች ከአንድ ሳምንት በኋላ የወጣ ነው። 

ሀገሪቱ እገዳውን የጣለችው፤ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ “ከባድ እና አሉታዊ መዘዞች ሊያስከትሉ ይችላሉ” የተባሉ ሰዎች ቪዛ የሚከለከሉበትን ህግ በመጥቀስ ነበር። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ቶሚ ፒጌት በወቅቱ ባወጡት መግለጫ፤ “በቀጠናው ያለውን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥሉ የህወሓት ባለስልጣናት እና ሌሎች ግለሰቦችን ለማጋለጥ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያሉትን መሳሪያዎች ሁሉ እንጠቀማለን” ማለታቸው ይታወሳል።

የዛሬው የአሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ ህወሓትን በቀጥታ ባይጠቅስም፤ “ሆነ ብለው” የሰላም ሂደቶችን “የሚያደናቅፉ” አካላት የሚል አገላለጽ ተጠቅሟል። በክልሉ ያሉ የፖለቲካ እና የሲቪል ማህብረሰብ መሪዎችም፤ “በፖለቲካዊ ውይይት” መሳተፍ እንደሚገባቸውም ኤምባሲው በመግለጫው አሳስቧል። 

መሪዎቹ በጥቅምት 2015 በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመውን የግጭት ማቆም ስምምነት “ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ” ማድረጋቸው “እጅግ አስፈላጊ” መሆኑንም ኤምባሲው አስገንዝቧል። አሜሪካ ይህን ብትልም የትግራይ ክልልን በአሁኑ ወቅት እያስተዳደረ ያለው ህወሓት፤ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት “መፍረሱን” በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ሲያስታውቅ ቆይቷል።

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ መቐለ ተጉዘው ከህወሓት ሊቀመንበር እና ከወቅቱ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በተነጋገሩበት ወቅት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል፤ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት አፈጻጸም አንዱ እንደነበር ተገልጿል። የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲፈረም ቁልፍ ሚና ከተጫወቱ አሸማጋዮች አንዱ የሆኑት ኦባሳንጆ፤ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ናቸው።

በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው የትግራይ የሰላም ሂደት ድጋፏን ስትሰጥ የቆየችው አሜሪካ፤ በዛሬው የኤምባሲ መግለጫዋም ይህንኑ አስተጋብታለች። የሰላም ሂደቶችን “የሚያደናቅፉ” አካላት በህብረቱ ለሚመሩ የውይይት ጥረቶች በ“አስቸኳይ ትብብር” እንዲያደርጉም አሳስባለች።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በቀጣይ ጊዜያት በትግራይ በሚያደርገው ጉብኝት፤ ከአካባቢው መሪዎች እና ሰብአዊ እርዳታ ከሚያከናውኑ አካላት ጋር የመወያየት እቅድ እንዳለውም በመግለጫው ላይ ሰፍሯል። ሆኖም ጉብኝቱ መቼ እንደሚካሄድ በመግለጫው አልተጠቀሰም። 

የኤምባሲው መግለጫ ዩናይትድ ስቴትስ ለትግራይ ክልል የሚደረጉትን “ወሳኝ የሆነ” የነፍስ አድን ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን እንደምትደግፍም ጨምሮ አመልክቷል። ቀጠናው የሚኖረው የረጅም ጊዜ መረጋጋት፤ የአካባቢው ማህበረሰቦች “ከአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ተቀባይነት ራስን ወደ መቻል እንዲሸጋገሩ እና ችግርን የመቋቋም አቅም እንዲያጠናክሩ ያደርጋል” ሲልም ኤምባሲው መግለጫውን አጠቃልሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)