ተቃዋሚ ፓርቲዎች 40 የፓርላማ መቀመጫዎችን አሸነፉ

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 40፣ የግል ዕጩዎች ደግሞ 8 የፓርላማ መቀመጫዎች ማሸነፋቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አደረገ። ከሶስት ሳምንት በፊት በተካሄደው በዚህ ምርጫ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን 438 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ መቆጣጠሩንም ቦርዱ አስታውቋል። 

ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው፤ ዛሬ እሁድ ሰኔ 14፤ 2018 በአዲስ አበባው ስካይላይት ሆቴል ባካሄደው የምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሃ ግብር ነው። ቦርዱ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤትን ይፋ ያደረገው፤ በምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ካስቀመጠው ዕለት 10 ቀናት ዘግይቶ ነው።

የአሸናፊ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የግል ተወዳዳሪዎች ስምና ለየምክር ቤቱ ያሸነፉትን መቀመጫ ብዛት የያዘ ይፋዊ መግለጫ ከምርጫ ቀን ቀጥሎ ባሉት 10 ቀናት ውስጥ ቦርዱ ማውጣት እንዳለበት በህግ ተደነግጓል። ይህ የሚደረገው ግን “ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር” እንደሆነም በ2011 ዓ.ም. በወጣው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ላይ ሰፍሯል። 

በዚህ መሰረት ምርጫ ቦርድ በማዕከል ደረጃ ያረጋገጣቸውን የተወሰኑ የምርጫ ውጤቶችን በየጊዜው ሲያሳውቅ ቆይቷል። ቦርዱ እስከ ትላንት በስቲያ  ድረስ ይፋ ካደረጋቸው 96 የፓርላማ መቀመጫ ውጤቶች ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሸነፉት የፓርላማ መቀመጫ ብዛት 19 ነበር። 

እስከ አርብ ሰኔ 12 ይፋ በተደረጉ ውጤቶች፤ የግል ዕጩዎች ያገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት 4 እንደሆነ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በአንጻሩ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በእነዚህ የውጤት ማሳወቂያ ጊዜያት እንዳሸነፋቸው የተገለጹ የፓርላማ ወንበሮች ብዛት 73 ነው።

ምርጫ ቦርድ በዛሬው ዕለት ይፋ ባደረገው አጠቃላይ የምርጫ ውጤት፤ ብልጽግና ፓርቲ 438 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ማሸነፉ ተገልጿል። በአጠቃላይ የምርጫ ውጤቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 40 የፓርላማ ወንበሮች ማግኘታቸውን ቦርዱ በዛሬው መርሃ ግብሩ አስታውቋል።

በግንቦቱ ምርጫ በተወዳደሩባቸው ቦታዎች ከፍተኛ ድምጽ አግኝተው ወደ ፓርላማ የሚገቡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት 16 ነው። ከእነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 13 የተወካዮች ምክር ቤት በማግኘት ቀዳሚ ሆኗል።

ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ እና በአራት ክልሎች ዕጩ ተወዳዳሪዎቹን ለፓርላማ አስመርጧል። የፖለቲካ ፓርቲው 7 የፓርላማ መቀመጫዎችን ያገኘው ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ነው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተወዳደሩት የፓርቲው መሪ ኢዮብ መሳፍንት ለፓርላማ መመረጣቸውን ምርጫ ቦርድ ቀደም ብሎ አሳውቆ ነበር።  

የአማራ ህዝብ ንቅናቄ (አብን) ስድስት መቀመጫዎችን በማግኘት ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። አብን ሁሉንም መቀመጫዎች ያገኘው ከአማራ ክልል ነው። የፖለቲካ ፓርቲው ለፓርላማ ካስመረጣቸው ተወዳዳሪዎቹ መካከል ሊቀመንበሩ አቶ በለጠ ሞላ ይገኙበታል።

ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እያንዳንዳቸው ሶስት መቀመጫዎች በማግኘት የሚከተሉት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)፣ ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴሃን) ናቸው። መድረክ ሶስቱንም መቀመጫዎች ያሸነፈው በሲዳማ ክልል ሲሆን አዴሃንም በተመሳሳይ በአማራ ክልል ያቀረባቸው ሶስት ተወዳዳሪዎቹ ለፓርላማ ተመርጠውለታል።

ከድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ከሀረሪ እና ጋምቤላ ክልሎች አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪ ለፓርላማ አልተመረጠም። እነዚህን ክልሎች ጨምሮ  በአማራ፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተወዳዳደሩ የግል ዕጩዎች የፓርላማ ወንበር ማግኘት አልቻሉም።

በዛሬው ውጤት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመረጣቸው ይፋ ከተደረገ ስምንት የግል ዕጩዎች መካከል አምስቱ የተወዳደሩት በኦሮሚያ ክልል ነበር። ከእነዚህ ተወዳዳሪዎች መካከል የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እና ዶ/ር ዲማ ነገዎ ለፓርላማ ሲመረጡ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ የቁጥር ማስተካከያ ተደርጎበታል]