የብሪክስ ሀገራት ያቋቋሙት የልማት ባንክን፤ ኢትዮጵያ በአባልነት እንድትቀላቀል የሚያስችላት የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራ። ረቂቅ አዋጁ በፓርላማ ጸድቆ ለባንኩ የገዢዎች ቦርድ ሲገባ፤ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ እና አልጄሪያ በመቀጠል አራተኛዋ አፍሪካዊት የልማት ባንኩ አባል አገር ትሆናለች።
ዋና መስሪያ ቤቱን በቻይና ሻንጋይ ከተማ ያደረገው የብሪክስ የልማት ባንክ፤ “ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ” በሚል ስያሜ የሚጠራ ነው። ይህንን ባንክ ኢትዮጵያ በአባልነት መቀላቀሏ “ለሀገራዊ የልማት ፋይናንስ፣ ለመሰረተ ልማት ድጋፍ እና ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን ለማግኘት” ያስችላታል ተብሎ እንደታመነበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በቀድሞዋ የብራዚል ፕሬዝዳንት ዲልማ ሮዜፍ የሚመራው “ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ” ባንክ፤ “ታዳጊ ሀገራት ለሚያከናውኗቸው የመሰረተ ልማት እና የዘላቂ ልማት ዕቅዶች” የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ የተቋቋመ ነው። በ100 ቢሊዮን ዶላር የተፈቀደ እና በ52.7 ቢሊዮን ዶላር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው ይኸው ባንክ፤ ከሻንጋይ በተጨማሪ በብራዚሏ ሳኦ ፖሎ እና በህንድ ጉጅራት ከተሞች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አሉት።

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የባንኩ መስራች አባላት ሲሆኑ፤ ባንግላዴሽ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ግብጽ፣ አልጄሪያ እና ኡዝቤኪስታን ባለፉት አምስት ዓመታት ባንኩን በአባልነት ተቀላቅለዋል። የ“ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ” የገዢዎች ቦርድ በዕጩ አባልነት ከተቀበላቸው አራት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች። ሀገሪቱ “ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ” መሥራች የሆነው የብሪክስ ስብስብ አባል ለመሆን የበቃችው በታህሳስ 2016 ዓ.ም. ነበር።
የባንኩ አባልነት ኢትዮጵያ “ከደቡብ ደቡብ የፋይናንስ ስርዓቶች ጋር የሚኖራትን ትስስር” የሚያጠናክር መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በዛሬው መግለጫው አመልክቷል። ይህንን መሰረት በማድረግም ኢትዮጵያ የባንኩ አባል እንድትሆን የሚያስችላት የአዋጅ ረቂቅ መዘጋጀቱን ጽህፈቱ ቤቱ ጠቁሟል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ አርብ ሰኔ 19፤ 2018 ባካሄደው መደበኛ ስብስባው፤ በዚህ አዋጅ ረቂቅ ላይ መወያየቱን ጽህፈት ቤቱ አክሏል። ምክር ቤቱ በአዋጁ ላይ “በሰፊው” ከተወያየ በኋላ “ግብአቶችን በማከል” ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑንም ጽህፈቱ ቤቱ ገልጿል።(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































