ለአምስት ቀናት በእስር ያሳለፈው ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ በፍርድ ቤት በተወሰነው መሠረት በዋስትና እንዲፈታ የተደረገው ጥረት አልተሳካም። የአዲስ አበባ ሰበር ሰሚ ችሎት ፖሊስ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ ካደረገ በኋላ ተስፋለም እንዲፈታ የተሰጠውን ትዕዛዝ ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን፤ 2017 ከቀኑ 9:00 ሰዓት ጀምሮ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለማስረከብ ቢሞከርም ተቀባይ አልተገኘም። በዚህም ምክንያት ተስፋለም ይህ መግለጫ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ ከእስር አልተፈታም።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስን ለፌድራል ፖሊስ የማስረከብ ፍላጎት እንዳለው ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተገንዝቧል።
ተቋማችን የተስፋለም ወልደየስ የዋስትና መብት እንዲከበር በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ቂርቆስ ምድብ ችሎት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እና የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ችሎት የተላለፉ ውሳኔዎች ገቢራዊ እንዲሆኑ አበክሮ ይጠይቃል። ከዚህ በተጨማሪ የፍትህ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ተቋማት እና ግለሰቦች የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲከበር ጥሪያቸውን እንዲያቀርቡ እንጠይቃለን።































