አሜሪካ በህወሓት አመራሮች ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የጣለችው የቪዛ እገዳ፤ የትኛውን የሀገሪቱን ህግ የተመረኮዘ ነው?

አሜሪካ “አክራሪ” ባለቻቸው በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አባላት እና በቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ገደብ መጣሏን በዛሬው ዕለት አስታውቃለች። የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በግለሰቦቹ ላይ እርምጃውን የወሰደው፤ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ “ከባድ እና አሉታዊ መዘዞች ሊያስከትሉ ይችላሉ” የተባሉ ሰዎች ቪዛ የሚከለከሉበትን ህግ በመጥቀስ ነው። 

ይህ ህግ በ1944 ዓ.ም በሀገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት የወጣው “የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አዋጅ” ነው። ህጉ በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የቪዛ ገደብ የመጣል ስልጣንን ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሰጣል። የውጭ ዜጎች የአሜሪካ ቪዛ ለማግኘትም ሆነ ወደ ሀገሪቱ ለመግባት በምን ምክንያቶች ገደብ ሊጣልባቸው እንደሚችል በዚህ አዋጅ ላይ ተዘርዝሯል።

በአዋጁ ከተዘረዘሩ ምክንያቶች መካከል “የጸጥታ እና ተያያዥ ምክንያቶችን” የሚመለከተው ክፍል ይገኝበታል። በህወሓት አባላት ላይ የተጣለውን የቪዛ ገደብ በሚመለከት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቃባይ ቶሚ ፒጌት አማካኝነት የተሰራጨው መግለጫ፤ ይህንን የአዋጅ ክፍል ያጣቀሰ ነው።

ይኸው የአዋጁ አንቀጽ “[የአሜሪካ] የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መግባት ወይም ሊያከናውናቸው ያቀዳቸው ተግባራት ለዩናይትድ ስቴትስ ‘ከባድ አሉታዊ የውጭ ፖሊሲ መዘዞች ሊያስከትል ይችላል’ ብለው ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት ካላቸው፤ ግለሰቡ ወደ ሀገር እንዳይገባ ይከለከላል” ሲል ይደነግጋል።

በአዋጁ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የወሰዱት እርምጃ፤ “በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ረገድ ተጠያቂ የሆኑትን ወይም ተባባሪ የሆኑ ግለሰቦችን” የሚመለከት እንደሆነ በመስሪያ ቤታቸው መግለጫ ላይ ሰፍሯል። ሆኖም መግለጫው የቪዛ ገደብ ሊጣልባቸው የሚችሉ ግለሰቦችን ማንነት በዝርዝር አልገለጸም።

የሩቢዮ እርምጃ ይፋ የሆነው፤ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው። ይህ ውጥረት በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ጦርነት “ዳግም ይቀሰቅሳል” የሚል ስጋት እንደፈጠረ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለዚህ በማሳያነት የጠቀሰው፤ ባለፈው ጥር ወር በትግራይ ጸጥታ ኃይሎች  (TSF) እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ነው። የመስሪያ ቤቱ ቃል አቃባይ ቶሚ ፒጌት ይህንን ግጭት፤ ከትግራዩ የሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ የተካሄደ “የመጀመሪያው ቀጥተኛ ውጊያ” ሲሉ ጠርተውታል።

ቃል አቃባዩ የጠቀሱት ግጭት የተካሄደው፤ የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በሚወዛገቡበት ጸለም/ጠለምት አካባቢ ነበር። ግጭቱ የተቀሰቀሰው የትግራይ ኃይሎች ወደ እዚህ አካባቢ መግባታቸውን ተከትሎ ነው። በወቅቱ የትግራይ ኃይሎች ከመከላከያ ሰራዊት እና በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ሚሊሺያዎች ጋር ለቀናት የዘለቀ ውጊያ አካሄደዋል።

ውጊያውን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቐለ፣ አክሱም እና ሽረ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ማቋረጡ አይዘነጋም። ይህ ውጊያ የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ኃይሎችን “ወደለየለት ጦርነት ያስገባል” የሚል ስጋት በወቅቱ አሳድሮ ነበር። 

ከዚያ በኋላ በነበሩት ወራት የተካሄዱ መለስተኛ ግጭቶች እና የድሮን ጥቃቶች ስጋቱን ይበልጥ አባብሰውታል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቃባይ በዛሬው መግለጫቸውም፤ በሰሜን ኢትዮጵያ “ወደ ጦርነት እንመለሳለን” በሚል ፍርሃት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች “ከቤታቸው መሰደዳቸውን”  በአጽንኦት አንስተዋል።

አሜሪካ የትግራይ ህዝብን ጨምሮ “በሰላም እና በክብር መኖር ከሚፈልጉ” የኢትዮጵያ ህዝቦች ጎን መቆሟን እንደምትቀጥል በመግለጫቸው የጠቆሙት ቃል አቃባዩ፤ ከዚህ በተቃራኒ በሚቆሙ ወገኖች ላይ ሀገራቸው በቀጣይነት የምትወስደው እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል። “በቀጠናው ያለውን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥሉ የህወሓት ባለስልጣናት እና ሌሎች ግለሰቦችን ለማጋለጥ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያሉትን መሳሪያዎች ሁሉ እንጠቀማለን” ሲሉ ቶሚ ፒጌት አስጠንቅቀዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ተጽዕኖ ለማሳደር እንደ መሳሪያ የምትጠቀምበት የቪዛ እገዳን፤ በህወሓት ባለስልጣናት ላይ ስትጥል የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከአምስት ገደማ ዓመት በፊት በህወሓት ባለስልጣናት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰዱት፤ በዛሬው መግለጫ የተጠቀሰውን የኢሚግሬሽን እና የዜግነት ሕግ አንቀጽ በማጣቀስ ነበር። 

ብሊንከን በግንቦት 2013 ዓ.ም. የጣሉት የቪዛ እገዳ፤ ህወሓትን ጨምሮ በወቅቱ በትግራይ የነበረውን “ቀውስ” ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት “በማደናቀፍ” “ተጠያቂነት ያለባቸው” ወይም “ተባባሪ የሆኑ” በሚል በተለዩ ኃይሎች ላይ ነው። የትግራይ ጦርነት በተቀሰቀሰ በሰባተኛው ወር ገደማ የተጣለው ይህ እገዳ፤ ከህወሓት አባላት በተጨማሪ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ባለስልጣናትን እንዲሁም የአማራ ክልል ጸጥታ አስከባሪዎች እና ኢ-መደበኛ ኃይሎችን ያካተተ ነበር። 

ብሊንከን የቪዛ እገዳውን ከጣሉ ከሶስት ወራት ገደማ በኋላ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ህወሓትን ጭምር የሚመለከት ማዕቀብ ጥለዋል። በወቅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ተባብሶ በነበረው የሰብአዊ ቀውስ እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የተላለፈው የፕሬዝዳንቱ ማዕቀብ፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት፣ የኤርትራ ገዢ ፓርቲ እንዲሁም የአማራ ክልል መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ ኃይሎች ላይም የተጣለ ነበር።

ማዕቀቡ በሰሜን ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ለነበረው “ቀውስ መባባስ አስተዋጽኦ ያደረጉ” ወይም “ቀውሱን ለመፍታት የሚደረገውን የተኩስ አቁም እና የሰላም ሂደት ያደናቀፉ” ግለሰቦች ጥሪት እንዳይንቀሳቀስ ትዕዛዝ የተላለፈበት ነበር። ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዙ ካነጣጠረባቸው ግለሰቦች መካከል የህወሓት አመራሮች ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)