በኢትዮጵያ የሚከሰቱ “ግጭቶች”፣ “የጸጥታ እና ደህንነት ስጋቶች”፤ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዋነኛ ምክንያት ሆነው መቀጠላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ 

የአማራ እና ትግራይ ክልሎችን ጨምሮ በሰባት የሀገሪቱ ክልሎች የሚከሰቱ “ግጭቶች”፣ “የጸጥታ እና ደህንነት ስጋቶች”፤ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዋነኛ ምክንያት ሆነው መቀጠላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። ኮሚሽኑ በአራት ክልሎች ውስጥ ባሉ “በርካታ አካባቢዎች” “የዘፈቀደ እስር እየተፈጸመ” መሆኑንም ገልጿል።

ኮሚሽኑ እነዚህን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፋ ያደረገው፣ ለፓርላማ ባቀረበው የ11 ወራት የስራ ክንውን እና የሀገራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን በዳሰሰ አንኳር ሪፖርቱ ነው። ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢሰመኮ፤ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን እና የኮሚሽኑን የስራ አካሄድ የተመለከተ ሪፖርት ለፓርላማ እንደሚያቀርብ በ2012 እንደገና በወጣው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ተደነግጓል። 

በ14 ገጾች የተዘጋጀው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የዘንድሮው ሪፖርት፤ ግማሽ ያህል ክፍሉን የሸፈነው በሀገሪቱ ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ነው። ኢሰመኮ “ክፍተቶች እና ተግዳሮቶች” በዘረዘረበት የሪፖርቱ ክፍል፤ ከሰብዓዊ መብቶች ማስፋፋት እና ጥበቃ አንጻር “አጠቃላይ አንድምታ አለው” ያላቸውን ሁለት ጉዳዮች ጠቅሷል።

የመጀመሪያው በተለያዩ ክልሎች የሚከሰቱ “ግጭቶች” እንዲሁም “የጸጥታ እና ደህንነት ስጋቶችን” የሚመለከት ነው። በግጭት ቀጠናዎች ውስጥ እና ውጪ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚፈጽሙ አካላት ላይ “ተገቢውን ምርመራ አለማድረግ” እና “ተጠያቂነትን አለማረጋገጥ” ኮሚሽኑ በሁለተኛነት የጠቀሰው አንኳር ጉዳይ ነው።

ኢሰመኮ “ግጭቶች የሚከሰቱባቸው” በሚል በሪፖርቱ የዘረዘራቸው አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችን ነው። ኮሚሽኑ በዓመታዊ የሰብአዊ መብት ሪፖርቱ የጠቀሳቸው ክልሎች፤ በዚህ ዓመት በተለያዩ ጊዜያት ባወጣቸው መግለጫዎችም የተካተቱ ናቸው። 

ተቋሙ በእነዚህ መግለጫዎቹ በክልሎቹ በሚከሰቱ ግጭቶች እና የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል። ኢሰመኮ ባለፈው ታህሳስ ወር ባወጣው መግለጫ በጋምቤላ ከተማ እና በአካባቢው ወረዳዎች በተቀሰቀሰ ግጭት የሰው ሕይወት ማለፉን እና የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቆ ነበር።

ኮሚሽኑ ባለፈው ጥር ወር ባወጣው መግለጫ ደግሞ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች፤ “የሰዎችን ህይወት፣ የአካል ደህንነት፣ ነጻነት እና የንብረት መብቶች ስጋት ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች” መፈጠራቸውን ገልጿል። በየካቲት ወር በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን፣ ሽርካ፣ ጉና፣ መርቲ፣ አሰኮ እና ኦንቆሌ ዋቤ ወረዳዎች በተሰነዘሩ ጥቃቶች፤ በሰዎች ህይወት፣ አካል እና ንብረት አደጋ ላይ ጉዳት መድረሱን የሰብአዊ መብት ተቋሙ በወቅቱ አስታውቋል። 

ኢሰመኮ ለፓርላማ ባቀረበው የሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አንኳር ሪፖርቱ፤ በዚህ ዓመት በግጭቶች ሳቢያ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉም ሆነ እንደቆሰሉ አሃዛዊ መረጃ ሳያካትት ቀርቷል። በህይወት የመኖር መብትን በሚመለከተው የሪፖርቱ ክፍልም ኮሚሽኑ ዝርዝር መረጃ አላቀረበም። 

ተቋሙ ይህንን ላለማድረጉ የሰጠው ምክንያት፤ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ይፋ ባደረገው “አራተኛው ሀገራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ” “በህይወት የመኖር እና እና የአካል ደህንነትን” ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ መብቶችን የተመለከቱ ጉዳዮችን በዝርዝር ማቅረቡን ነው። በዚህ ሪፖርት ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የህይወት መብት ሁኔታ “አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን” የሚያሳዩ በርካታ ክስተቶች መስተዋላቸውን ኢሰመኮ አስታውቆ ነበር።

በእነዚህ ክስተቶች ሳቢያ በሰባት ክልሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ኮሚሽኑ በዚሁ ዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ ጠቅሶ ነበር። ሪፖርቱን በወቅቱ ይፋ ያደረጉት፤ በጥር 2017 ዓ.ም. ኢሰመኮን በዋና ኮሚሽነርነት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ብርሃኑ አዴሎ ናቸው። 

አቶ ብርሃኑ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 16፤ 2018 በፓርላማ ተገኝተው በንባብ ያቀረቡት የሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አንኳር ሪፖርት፤ “መልካም እመርታዎችን፣ አሳሳቢ ጉዳዮችን እና ተግዳሮቶችን” ለማሳየት እንጂ “ጉዳዮቹን በተሟላ መልኩ የዳሰሰ” አለመሆኑን ገልጸዋል። ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መሰረታዊ ምክንያት የሆኑ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ “ለግጭቶች ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግም” ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። 

መንግስታዊውን የሰብዓዊ መብት ተቋም ከአቶ ብርሃኑ በፊት የመሩት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ ለፓርላማ ያቀርቧቸው በነበሩ ሪፖርቶች ጭምር መንግስትን ጭምር ተጠያቂ የሚያደርጉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ የማድረግ አካሄድን ይከተሉ እንደነበር አይዘነጋም። የቀድሞው ኮሚሽነር በ2014 ዓ.ም. ግንቦት ወር ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች “እጅግ አሳሳቢ” ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር።

ከእነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል በመንግስት የጸጥታ አካላት የተፈጸሙ ከፍርድ ውጭ የሆኑ ግድያዎች (extra-judicial killings) እና ከመጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም (excessive use of lethal weapons) እንደሚገኙበት ዶ/ር ዳንኤል በዚሁ የፓርላማ ቆይታቸው መናገራቸው ይታወሳል። የቀድሞው ኮሚሽነር በዚሁ ሪፖርታቸው፤ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ የሚፈጸም የዘፈቀደ እስር (arbitrary arrest) እና የተራዘመ የቅድመ-ክስ እስር በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም አልሸሸጉም።

ከአራት ዓመት በኋላም የዘፈቀደ እስር አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሆኖ መቀጠሉ በኢሰመኮ የዘንድሮ ሪፖርት ላይ ተመላክቷል። ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚገኙ አካባቢዎች የዘፈቀደ እስር እየተፈጸመ መሆኑን መገንዘቡን በሪፖርቱ አስታውቋል። 

ሰዎች ለእስር የሚዳረጉት “የወንጀል ተጠያቂነት በሌለባቸው”፣ “የውል ግንኙነትን መሰረት ባደረጉ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች” እና “የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ በሌለባቸው ሁኔታዎች” እንደሆነ ኢሰመኮ በሪፖርቱ ዘርዝሯል። የብድር ገንዘብ መመለስ ባለመቻል፣ የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ እና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ክፍያን በወቅቱ ባለመክፈል ምክንያት የዘፈቀደ እስር እንደሚፈጸምም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አክሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)