ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች “የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ” ለማካሄድ እና “ተቃውሞን ለመቅጣት ስልጣን ይሰጣል” ያለውን በትግራይ ክልል ስራ ላይ የዋለ ህግ እንዲሻር ለክልሉ ባለስልጣናት ጥሪ አቀረበ። የትግራይ ክልል ምክር ቤት ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ስራ ላይ ያዋለው ህግ፤ “ኤርትራ ከምትከተለው አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት ጋር ምስስሎሽ ያለው ነው” ሲልም ድርጅቱ ተችቷል።
መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ሂውማን ራይትስ ዎች ባለፉት ሳምንታት አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተውን ህግ በተመለከተ ጠንከር ያለ ጥሪ ያቀረበው ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 16፤ 2018 ባወጣው መግለጫ ነው። “የትግራይን ህዝብ ህልውና እና ደህንነት ለማረጋገጥ” ያለመ ነው የተባለለት ይህ ህግ፤ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ትችቶች ሲቀርቡበት ቆይተዋል።
ሂውማን ራይትስ ዎች ዛሬ ባወጣው መግለጫ ህጉ “አላግባብ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ እና ግልጽ ያልሆኑ አገላለጾች” ያሉበት እና “በተለያዩ ጥፋቶች” የተወነጀሉ ሰዎችን በሞት የሚያስቀጣ አንቀጾችን ያካተተ እንደሆነ ገልጿል። የድርጅቱ የአፍሪካ ክፍል ምክትል ኃላፊ ላቴሺያ ባድር፤ የትግራይ ባለስልጣናት በክልሉ ለቀጠለው ፖለቲካዊ ውጥረት “ሲቪል ሰዎችን ለውትድርና በመመልመል እና የሚቃወሙትን በመቅጣት” ምላሽ መስጠት እንደማይገባቸው አሳስበዋል።
በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ካለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ፤ በውጊያ ሊሳተፉ የሚችሉ ወጣቶችን በግዳጅ የመልመል እና በአፈሳ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የማጋዝ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ እንደነበር የሀገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና መገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል። እነዚህን ይፋዊ ሪፖርቶች በዛሬው መግለጫው ላይ የጠቀሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ ቤት ለቤት በሚደረግ አሰሳ ህጻናት ጭምር ለወታደራዊ ግዳጅ እየተመለመሉ መሆኑን አስታውቋል።
ከግዳጅ ምልመላ በሚያመልጡ ሰዎች ምክንያት በየአካባቢው ያሉ ባለስልጣናት እና የትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ቤተሰቦቻቸውን እንደሚቀጡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ መረጃ እንደደረሰው ገልጿል። የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እና ዳግም የሚቀስቅስ ግጭትን በመፍራት፤ በርካታ ወጣቶች ከክልሉ እየሸሹ መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች በዛሬው መግለጫው አመልክቷል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ የጸደቀው ህግ፤ ዕድሜያቸው እና ጤናቸው የሚፈቅድላቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ሁሉ “በግዳጅ በወታደርነት የሚመለመሉበትን ማዕቀፍ ያስቀምጣል” ሲል በዛሬው መግለጫው ላይ አስፍሯል። በዚሁ ህግ ላይ የተካተቱ በሞት የሚያስቀጡ ጥፋቶች “አሻሚ እና ለትርጉም ክፍት ናቸው” ሲል ድርጅቱ ተችቷል።

በሞት ያስቀጣሉ በሚል በህጉ ከተጠቀሱ ጥፋቶች መካከል “በስትራቴጄካዊ የመከላከያ አቅርቦቶች ላይ ጉዳት ማድረስ” የሚለው ይገኝበታል። የትግራይ ክልል “ሰላምን እና ጸጥታ አደጋ ላይ መጣል” እና “ከጠላት ጋር መተባበርም” በህጉ ተመሳሳይ ቅጣት የሚያስከትሉ ናቸው።
የትግራይ ክልልን “አንድነት እና ግዛት ማዳከም” የሚለው ጥፋትም እንደዚሁ በሞት የሚያስቀጣ ነው። ይህ ቅጣት ተግባራዊ የሚደረገው በማንኛውም ሀገር ዜጋ ላይ እንደሚሆን ህጉ ይደነጋግል። በማንኛውም ሁኔታዎች ውስጥ የሚፈጸምን የሞት ቅጣት አጥብቆ እንደሚቃወም ሂውማን ራይትስ ዎች በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ሌላው በመግለጫው የተቸው፤ ከምልመላ የሚሸሹ እና ከወታደራዊ አገልግሎት የሚከዱ ሰዎችን በወንጀል እንዲጠይቁ የሚያደርገውን የህጉን ክፍል ነው። በዚህ ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰቦች እስከ 50 ሺህ በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልባቸው መግለጫው ጠቁሟል።

የወታደራዊ ምልመላ ዘመቻን የሚተቹ እና ተቃውሞ እንዲደረግበት የሚቀሰቅሱ ሰዎች እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት የሚቀጣው የህጉ ክፍልም በሂውማን ራይትስ ዎች ተተችቷል። በህጉ የተካተተው የወታደራዊ ምልመላ ስርዓት፤ ከኤርትራ ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ጋር “አሳሳቢ ተመሳሳይነቶች” እንዳሉት ድርጅቱ ገልጿል።
“የትግራይ ባለስልጣናት የክልሉ ተጋላጭ ህዝብን ወታደራዊ አላማቸውን እንዲደግፍ ማስገደድ ወይም ለተጨማሪ በደል ማጋለጥ የለባቸውም” ሲሉ የድርጅቱ የአፍሪካ ክፍል ምክትል ኃላፊ ላቴሺያ ባድር አሳስበዋል። ኃላፊዋ ዳግም ሊፈጸም የተቃረበውን “የግፍ አዙሪት” ለማስቀረት ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግስታት ያላቸውን ተሰሚነት እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ይታከልበታል]































