የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ጠዋት የተወያየበት የብድር ስምምነት ከሰዓት በፓርላማ ጸደቀ 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ከሰዓት ባካሄደው ልዩ ስብሰባ፤ የዓለም ባንክ አካል ከሆነው ዓለም አቀፍ የልማት ማህበር የተገኘውን 600 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አጸደቀ። የብድር ስምምነቱን የያዘ የአዋጅ ሰነድ ለፓርላማ አባላት የተላከው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ከማሳለፉ አስቀድሞ ነው። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የፊርማ ስምምነት የተደረገባቸውን ሶስት የብድር ስምምነቶች የተመለከተው፤ ዛሬ አርብ ሰኔ 19፤ 2018 ጠዋት ባካሄደው መደበኛ ስብስባ ላይ ነው። ምክር ቤቱ በዚሁ ስብሰባው፤ ሶስቱ የብድር ስምምነቶች ከኢትዮጵያ “የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን” ማረጋገጡን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። 

የብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ምክር ቤቱ “በሙሉ ጽምጽ” የወሰነው ዛሬ ጠዋት ቢሆንም፤ ሰነዶቹ የፓርላማ አባላት እጅ የገቡት ግን ትላንት ከሰዓት እንደሆነ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጣለች። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እነዚህ አዋጆችን መርምሮ ለማጽደቅ በዛሬው ዕለት “ልዩ ስብሰባ” እንደሚያካሄድ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ላይ ያሳወቀውም ትላንት አመሻሽ ላይ ነበር።

በዛሬው “ልዩ ስብሰባ” ከቀረቡት ሶስት ስምምነቶች መካከል፤ የመጀመሪያው “ለዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ” የሚውል 600 ሚሊዮን ዶላር ብድርን የያዘ ነው። ይህ ብድር፤ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰዳቸውን “የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን ለመደገፍ” የዓለም ባንክ ለመስጠት የተስማማው 1.45 ቢሊዮን ዶላር የቀጥታ በጀት ድጋፍ አካል ነው። 

የባንኩ የገንዘብ ድጋፍ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በፋይናንስ እና ንግድ፣ በፊስካል ግልጽነት እና ዘላቂነት፣ በማህበራዊ እና አየር ንብረት እንዲሁም በኢነርጂ፣ መሰረተ ልማት እና ግብርና ግብዓት ገበያ ዘርፎች “የወሰዳቸውን እና በቀጣይ የሚተገብራቸውን ማሻሻያዎች ለማበረታታት” የቀረበ እንደሆነ ተገልጿል። በሁለት ዙር ፈሰስ የሚደረገው ይህ የገንዘብ ድጋፍ፤ በእርዳታ እና በብድር መልክ የሚሰጥ እንደሆነ ለፓርላማ አባላት በተሰራጨ ሰነድ ላይ ተመልክቷል። 

የዓለም ባንክ በእርዳታ መልክ ለመስጠት የተስማማው የገንዘብ መጠን 850 ሚሊዮን ዶላር ነው። ከዚህ የገንዘብ መጠን ውስጥ 200 ሚሊዮን ዶላሩ ያህሉ የተገኘው በተቋሙ “የአስቸኳይ ምላሽ መስጫ መስኮት” (crisis response window) አማካኝነት ነው። ባንኩ “የአስቸኳይ ምላሽ መስጫውን” የሚጠቀመው፤ “አስከፊ የተፈጥሮ አደጋ”፣ “ድንገተኛ የህዝብ የጤና አደጋዎች” አሊያም “የኢኮኖሚ መዋዠቆች” ለሚያጋጥማቸው ሀገራት እንደሆነ ከተቋሙ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለኢትዮጵያ ለመስጠት ስምምነት ላይ ከደረሰበት አጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ ቀሪው 600 ሚሊዮን ዶላር የሚለቀቀው በብድር መልክ ነው። በእርዳታ የሚገኘው ገንዘብ “ሙሉ ለሙሉ ወደ መንግስት ግምጃ ቤት (treasury) ፈሰስ ተደርጎ የፌዴራል በጀትን በቀጥታ ለመደገፍ እንደሚውል” “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ለፓርላማ አባላት የተሰራጨው ሰነድ ያብራራል።

የፌደራል መንግስት ለቀጣዩ 2019 ካዘጋጀው 2.34 ትሪሊዮን ብር በጀት ውስጥ 17 በመቶውን ለመሸፈን ያቀደው ከውጭ ሀገር ከሚያገኛቸው እርዳታ እና ብድሮች ነው። በ2019 በጀት ዓመት ከውጭ ሀገር “የልማት አጋሮች” በብድር ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የገንዘብ መጠን 193.7 ቢሊዮን ብር ነው።

ከሶስት ሳምንት በፊት በፓርላማ ቀርበው የ2019 የበጀት ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ “ከልማት አጋሮች ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ ትብብር በማጠናከር የውጭ ሀብት አሰባሰብን ለማሻሻል” ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸው ነበር። ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው “ከልማት አጋሮች በበጀት ድጋፍ መልክ የሚገኙ የውጭ ሀብቶች ለበጀት መሸፈኛ [እንዲውል] በገቢ ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል” ብለዋል።

ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ በሚገባው የ2019 በጀት ዓመት፤ ከዓለም ባንክ በቀጥታ የበጀት ድጋፍ ለማግኘት የታቀደው የብድር መጠን 58.6 ቢሊዮን ብር ነው። በዚሁ ጊዜ ውስጥ በባንኩ ስር ካለው ዓለም አቀፍ የልማት ማህበር በብድር ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው 7.2 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የ2019 በጀት ዝርዝር ያሳያል። 

በዛሬው ዕለት በተካሄደው በፓርላማ “ልዩ ስብሰባ” በሁለት ተዐቅቦ፣ በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው ከዓለም አቀፍ ልማት ማህበር የተገኘ የ600 ሚሊዮን ብር ብድር፤ “ከወለድ ነጻ መሆኑ” ተገልጿል። ሆኖም የዓለም ባንክ “የብድሩን ገንዘብ በማስተዳደር” ለሚሰጠው አገልግሎት 0.75 ፐርሰንት “የአገልግሎት ክፍያ” እንደሚከፍልበት ለፓርላማ አባላት በተሰራጨው ሰነድ ላይ ሰፍሯል።

ይኸው ሰነድ፤ ጥቅም ላይ ባልዋለው የብድሩ ገንዘብ ላይ የዓለም ባንክ በሚወስነው መሰረት “በዓመት እስክ 0.50 ፐርሰንት የሚደርስ የግዴታ ክፍያ ሊከፈልበት” እንደሚችል አመልክቷል። የብድሩን አጠቃላይ ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ከፍሎ ለማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ መንግስት የተሰጠው የ31 ዓመታት ጊዜ ነው። ይህ ገደብ የስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን የሚያካትት እንደሆነ በብድር ስምምነት ሰነዱ ላይ ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)