የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የግብር እፎይታ እንዲያደርግ የውሳኔ ሀሳብ ቀረበለት

በሐይማኖት አሸናፊ

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚደርሰውን ኢኮኖሚዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመቀነስ ለንግዱ ሕብረተሰብ የግብር ማቅለያ እንዲደረግ የውሳኔ ሃሳብ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ቀረበ። የውሳኔ ሀሳቡን ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ ነው።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው 10 ገጾች ያሉት የውሳኔ ሃሳብ የተዘጋጀው ወረርሽኙ በተለይም በዝቅተኛ የገቢ ደረጃ ላይ ያሉ ነጋዴዎች ላይ የሚያደርሰውን ኪሳራ እንዲቋቋሙ እና የከተማዋ ነዋሪዎች ላይም የኑሮ መወደድን ለመቀነስ ታስቦ እንደሆነ ያስረዳል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ ግብር ከፋዮች ላይ የተፈፃሚነት ወሰን የሚኖረው ይህ የውሳኔ ሀሳብ በደረጃ “ሀ” ፤ “ለ” እና “ሐ” ግብር ከፋዮች ላይ የሚተገበር እና የቫይረሱ ስርጭት እየታየ የሚሻሻል ነው።

የደረጃ “ሐ” ወይም አነስተኛ ግብር ከፋዮች ከሚያዚያ 1፤ 2012 እስከ ሰኔ 30፤ 2012 ላሉት ሶስት ወራት ከንግድ ትርፍ እና ከተርን ኦቨር ታክስ ግዴታ ነፃ እንዲደረጉ የውሳኔ ሃሳቡን ጠይቋል። በተጨማሪም ወደ ታክስ መረቡ የገቡ አዲስ ግብር ከፋዮች በዚህ ውሳኔ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሃሳቡን አቅርቧል።

ለውሳኔ ሀሳቡ መነሻ የሆነው የቁንጅና ሳሎን፣ ምግብ ቤቶች፣ ባርና ሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎች፣ የቤትና ህንጻ ኪራይ፣ የመኪና እና ማሽነሪ ኪራይ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጉዞ ወኪሎች፣ የመኝታ አገልግሎት እና በትራንስፖርት የተሰማሩ ዘርፎችን መንግስት ሊዘጋቸው የሚችላቸው ዘርፎች መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በመክተት መሆኑን ሰነዱ ያስረዳል።

ለደረጃ “ለ” ወይም መካከለኛ ግብር ከፋዮች መዝገብ የሚይዙ በመሆኑ በሚያቀርቡት መዝገብ ላይ ተመስርተው ግብራቸውን እንደሚከፍሉ ሰነዱ ይገልጻል። ግብር ከፋዮቹ በወረርሽኙ ምክንያት መዝገብ መያዝ ያልቻሉ ከሆነ፤ በቁርጥ ግብር ከሚጣልባቸው ግብር ላይ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ያለው የሶስት ወር የትርፍ ግብር እንዲቀርላቸው በውሳኔ ሀሳቡ ቀርቧል።

የደረጃ “ሀ” የግብር ከፋዮች ወይም ከፍተኛ የግብር ከፋዮችም በተመሳሳይ ሙሉ በሙሉ በመዝገብ ላይ የተመሰረቱ ግብር ከፋዮች በመሆናቸው በሚያቀርቡት መዝገብ መሰረት ግብራቸውን እንዲከፍሉ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ትካትቷል። በዚህ ደረጃ ውስጥ ሆነው መዝገብ ማቅረብ ላልቻሉ ግን በቁርጥ በሚወሰን ጊዜ የበጀት አመቱ የመጨረሻ ሶስት ወራት ላይ ከትርፍ ግብር ነፃ እንዲሆኑ እና ከደረጃ “ለ” ጋር ተመሳሳይ እፎይታ እንዲያገኙ ተጠይቋል።

ሰነዱ ከዚህ በሻገር የተለያየ አይነት የግብር እፎይታዎችን ለውሳኔ አቅርቧል። የአዲስ አበባ ከተማ የገቢዎች ቢሮ ለአስተዳደሩ ካቢኔ ለውሳኔ ካቀረባቸው ውስጥ የአከራይ ተከራይ ግብር፣ የገቢ ግብር፣ ምግብ ነክ አምራቾች የሚከፍሉትን ግብር፣ የፅዳት እቃ አምራቾች የሚከፍሏቸውን የግብር አይነቶች ጨምሮ በዘጠኝ አይነት የግብር አከፋፈል አይነቶች ላይ የተለያየ አይነት እፎይታ እንዲሰጥ የሚል ይገኝበታል።

የግብር እፎይታዎቹ ከጥቅምት 7፤ 2012 በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ በግብር አወሳሰን፣ በታክስ ኦዲት እና ምርመራ የስራ ክፍሎች የታክስ ውሳኔ ማሻሻያ ተደርጎባቸው፣ በማንኛውም የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ያሉ ግብር ከፋዮችን ከግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው፡፡

ግብር ከፋዮቹ ፍሬ ግብራቸውን ከሚያዚያ 2012 ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ከፍለው የሚያጠናቅቁ ከሆነ ወለድ እና መቀጮ እንዲነሳላቸው የከተማይቱ የገቢዎች ቢሮ ያዘጋጀው ሰነድ ጠይቋል። ፍሬ ግብራቸውን በስድስት ወር ከፍለው ማጠናቀቅ ላልቻሉ ግብት ከፋዮች ደግሞ ተጨማሪ ሶስት ወር የመክፈያ ግዜ ተሰጥቷቸው ዕዳቸውን ከከፈሉ መቀጫቸው እንዲነሳላቸውም ቢሮው ለከተማይቱ ካቢኔ የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

የውሳኔ ሃሳቡ ላይ ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስተያየታቸውን የሰጡት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኙ ጌታቸው ተክለማሪያም እርምጃው የከተማ አስተዳደሩን የሚያስመሰግን እና በጣም መልካም የሚባል እንደሆነ ገልጸዋል። ነገር ግን በተለይ በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው ለሚሰሩ ነጋዴዎች ከግብር እፎይታ ባሻገር ቀጥተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

“አብዛኛው በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው የሚሰሩ ዜጎች በዕለት ተዕለት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው ምክንያት ይህንን ወቅት እንዲቋቋሙ እና የሚቀንሱትን የሰው ሃይል ዝቅ ለማድረግ የሚያጡትን ገቢ መንግስት መሸፈን አለበት” ሲሉም ጌታቸው መደረግ ያለበትን ጠቁመዋል። “ባለቤቶችም ቢሆኑ ንግዳቸውን ዘግተው ያለ ገቢ ሊቀሩ ይችላሉ። ይህም ከወረርሽኙ ባሻገር ረሃብን ሊያስከትል ስለሚችል የፌደራል እና የከተማው አስተዳር በጋራ ቀጥታ የገንዘብ ድጎማ ሊደርጉላቸው ይገባል” ሲሉ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኙ አሳስበዋል።

የውሳኔ ሃሳቡ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ቀርቦ የሚጸድቅ ሲሆን ከመጽደቁ በፊት ማሻሻያዎች ሊደረጉበት እንደሚችሉም በከተማይቱ ገቢዎች ቢሮ ያሉ ምንጮቻችን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)