የችሎት ውሎዎች፦ በቀለ ገርባ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ ሂሩት ክፍሌ እና ሸምሰዲን ጣሃ

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ በተቀሰቀሰው ሁከት የተጠረጠሩ ፖለቲከኞችን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ በመመልከት ተጠምዶ ነበር የዋለው። ፍርድ ቤቱ ፒያሳ ከሚገኘው ነባሩ ችሎት በተጨማሪ ልደታ የሚገኘውን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዳራሽ በመጠቀም ጭምር ነበር የዛሬ ሰኞ ሐምሌ 20፤ 2012 ስራዎቹን ያከናወነው። 

ዛሬ ከሰዓት፤ በልደታው የተውሶ አዳራሽ የቀረቡት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፤ “ከህመምተኛ ልጃቸው ጋር እንዳይገናኙ በመከልከላቸው ለ3 ቀናት የረሃብ አድማ አድርገው እንደነበር” ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን ጠበቃቸው አቶ ቱሊ ባይሳ ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የአቶ በቀለን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ የተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት፤ 8 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ለፖሊስ መፍቀዱን ጠበቃቸው ገልጸዋል። ፖሊስ ፍርድ ቤቱን የጠየቀው 14 ቀናትን እንደነበርም ጠቁመዋል።

በእስር ላይ የሚገኙት ሌላኛው የኦፌኮ አመራር አቶ ደጀኔ ጣፋ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀጥሮ ቢኖራቸውም አለመቅረባቸው ታውቋል። የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ ሚልኪያስ ቡልቻ ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት አቶ ደጀኔ እና አቶ ኮርሳ ደቻሳ የተባሉ ተጠርጣሪ በኮሮና በሽታ ተይዘው በሆስፒታል ህክምና ላይ በመሆናቸው፤ ዛሬ በነበራቸው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል።

ፖሊስ አቶ ደጀኔን ጨምሮ በተመሳሳይ መዝገብ የተካቱቱ ሶስት ተጠርጣሪዎችን፤ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በአዲስ አበባ፣ ቡራዮ እና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ሁከት፤ “ተሳትፎ አላቸው” በሚል እንደጠረጠራቸው ለፍርድ ቤት አስታውቋል። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በዛሬው ችሎት የቀረቡት አቶ ሚሻ አደም ብቻ ናቸው። የሶስቱን ተጠርጣሪዎች የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ እየተመለከተ የሚገኘው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት፤ የ8 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ መፍቀዱን አቶ ሚልኪያስ ገልጸዋል። 

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በዛሬው ውሎው በሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ላይም ተመሳሳይ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። የስምንት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት የተሰጠባቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሂሩት ክፍሌ ናቸው።

የተጠርጣሪዋን ጉዳይ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፤ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጠናቅቆ እንዲያቀርብ ለሐምሌ 28፤ 2012 ቀጠሮ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ የሂሩት ጠበቃ ያቀረቡትን የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ ማደረጉንም ፓርቲያቸው አስታወቋል። 

የኢዜማ የሙያ ማኅበራት ተጠሪ የሆኑት ሂሩት በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት “በአዲስ አበባ ከተማ ከቅድስተ ማሪያም እስከ ግንፍሌ አካባቢ ያሉ ወጣቶችን በማስተባበር፤ ሁከት በማስነሳት ተሳትፈዋል” በሚል ተጠርጥረው ነው። ተጠርጣሪዋ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በመጀመሪያ የችሎት ውሏቸው ፖሊስ የጠየቀባቸው የ14 ቀናት የምርመራ ቀናት ተቀንሶ 10 ቀናት ተፈቅዶ ነበር። 

የጊዜ ቀጠሮ ጉዳዮችን የሚያስተናግደው የአራዳ ምድብ ችሎት በዛሬው ውሎው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ባልደረባ የነበሩት አቶ ሸምሰዲን ጣሃን ጉዳይም ተመልክቶ ነበር። ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ተጨማሪ 8 የምርመራ ቀናት መፍቀዱን ጠበቃ ሚልኪያስ ተናግረዋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)