በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የቅድመ ምርመራ ምስክር መስማት ተጀመረ

በሐይማኖት አሸናፊ

የፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ችሎት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ አቃቤ ህግ ያቀረባቸውን ምስክሮች መስማት ጀመረ። የሁለት ምስክሮችን ቃል በዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 14፤ 2012 ውሎው ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ፤ ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለመጪው ሰኞ ቀጥሯል።   

ዛሬ ከሰዓት በልደታ አዳራሽ የተሰመየው ችሎት፤ ወደ ምስክር መስማት ከመግባቱ በፊት ባለፈው ቀጠሮ የተሰጡ ትዕዛዞች መፈጸማቸውን አረጋግጦ አዳዲስ ትዕዛዞችን ሰጥቷል። ችሎቱ በቅድሚያ ያየው አቶ ጀዋር መሐመድ ህክምና እንዲያገኙ የሰጠው ትዕዛዝ መፈጸም፤ አለመፈጸሙን ነው።

አቶ ጃዋር ህክምና አለማግኘታቸውን እና ከትላንት ወዲያ ምሽት የጎበኟቸው አቃቤ ህግ እንዲታከሙ መፍቀዳቸውን ነገር ግን ይህ አለመፈጸሙን ገልጸዋል። ነገር ግን ሃኪማቸው በማግስቱ ጠዋት ሲመጡ እንዳይገቡ መደረጉን እና በተደጋጋሚም ሃኪማቸው ቢመጡም መግባት እንዳልቻሉ አመልክተዋል። የአቃቤ ህግ ትዕዛዝ ከላይ በመጣ ውሳኔ መቅረቱን መስማታቸውንም አክለዋል። አሁንም ህመም ላይ መሆናቸው የገለጹት አቶ ጃዋር ለደህንነታችው ሲባል ግን በግል ሃኪም ካልሆነ መታየት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

“እኔ የመንግስትን ተቋማት በመናቅ ወይም ሌላ ጥቅም ፈልጌ ሳይሆን ስጋት ስላለብኝ ነው። በመንግስት ውስጥ ያሉ ሰዎች በራሳቸው ወይም በሌሎች አካላት ተነሳስተው አደጋ ሊጥሉብኝ ይችላሉ። እኔ እዚህ ስመጣ እንኳን፤ ከፊት እና ከኋላ መትረየስ ተደግኖ ነው። እዚህ ፍርድ ቤት እኔ ስገባ እና ስወጣ ሰው የማይንቀሳቀሰው እኮ እዚህ አገር እንደኔ ስጋት ያለበት ሰው ስለሌለ ነው” ብለዋል።  

በሰልፎች ላይ “ሃጫሉ ሞቷል፤ ጃዋር ይቀራል” መባሉን ያነሱት አቶ ጃዋር በግል ሃኪም ካልሆነ እንደማይታዩ ገልጸዋል። አቶ ጀዋር ለፍርድ ቤቱ “ወደ ፊት ህሊናዬን ብስት እንኳን በመንግስት ህክምና ማግኘት አልፈልግም” ሲሉም አሳስበዋል።

የጎበኟቸው አቃቤ ህግ፤ “ ‘ህክምና አግኝቷል፤ አልታመም’ ብለው መግለጫ መስጠታቸውን ለፍርድ ቤቱ ያነሱት አቶ ጃዋር፤  “ይህ እጅግ አሳዝኖኛል” ብለዋል። “ከመኝታዬ ተነስቼ ነው ያነጋርኳቸው። እነሱን አናግሬ ስመለስም ታመሜ ነበር” ሲሉም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ለችሎት አስረድተዋል። 

በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን የሰጠው አቃቤ ህግ “የአቶ ጃዋር የመረጃ ምንጭ ምን እንደሆነ አላውቅም። ነገር ግን ‘አልታመሙም ወይም ህክምና አግኝተዋል’ የሚል መግለጫ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አልሰጠም” ሲል አስረድቷል። “ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል። የህመማቸውን ሁኔታ ላይ ጥርጣሬዎች አሉን አንጂ፤ እሳቸው አሉ የተባለው፤ አልተባለም” ሲሉም አስተባብሏል።

የህመሙ ሁኔታ ላይ ለጥርጣሬ መነሻ የሆነውን ምክንያት ያስረዱት ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ፍቃዱ ጸጋ፤ “እርሳቸው የማይሉትን እኮ ነው እህታቸው በመገናኛ ብዙሃን ‘ተመርዘዋል’ ሲሉ የነበረው። ይህም በ 12/12/ 12 ለተጠራው አመጽ ለማቀጣጣያ የታሰበ ያስመስለዋል” ብለዋል፡፡

በዕለቱም ምሽት የግል ሃኪማቸው እንዲያያቸው ሲጠየቁ፤ “ስልኩ አሁን የለኝም” ማለታቸውን እና ይህም ህመማቸው አጣዳፊ ከሆነ በሚል የተሰጠ ትዕዛዝ እንደነበር ፍቃዱ አስረድተዋል። በአለም አቀፍ መለኪያዎች መሰረት አንድ የተያዘ ሰው በፖሊስ የህክምና ተቋማት እርዳታ ማግኘት እና ከፍ ሲል ወደ ሲቪል የህክምና ተቋማት ሪፈር የሚባልበት ሂደት መኖሩን ያስረዱት አቶ ፍቃዱ፤ አቶ ጃዋር “እኔ በመረጥኩት ሃኪም ካልሆነ አልታከምም” ማለታቸው ግን “አግባብነት የለውም” ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጠው እና ትዕዛዙም ተላልፎለት የነበረው ፌደራል ፖሊስ በበኩሉ፤ ተጠርጣሪው በፈለጉት የግል ተቋም መታከም እንደሚችሉ ቢነገራቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ገልጿል። አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች በመንግስት የህክምና ተቋማት ህክምና ማግኘታቸውን ፖሊስ ገልጾ፤ “ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው” ሲል ተከራክሯል። አቶ ጃዋር የገለጹት የደህንነት ስጋትን በተመለከተ፤ የፌደራል ፖሊስ የበለጠ ስጋት እንዳለው እና ኃላፊነቱን ለመውሰድም የሚያመቸው በራሱ ተቋማት ከሆነ እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ትዕዛዙን በአጽንኦት ሰጥቷል። በህገ መንግስቱ አንቀጽ 21 መሰረት፤ ማንኛውም የተያዘ ሰው ህክምና የማግኘት መብት እንዳለው፤ ይህንን የማስፈጸም ግዴታ በአንቀፅ 13 ላይ መዘርዘሩን ገልጿል። በዚህ መሰረት በግል ሃኪማቸው እንዲታከሙ አዝዟል።

ፍርድ ቤቱ ባለፈው ችሎት በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የተካተቱ አምስት ተጠርጣሪዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ለሌሎች ተጠርጣሪዎችም ተመሳሳይ ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። በዛሬው የችሎት ውሎ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጃዋር መሐመድን ጨምሮ የአራት ተጠርጣሪዎችን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ውጤት አቅርቧል። በዚህም መሰረት ጃዋር፣ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ አዳነ (ሀምዛ ቦረና) እና ሸምሰዲን ጣሃ በተደረገላቸው ምርመራ ከኮሮና ቫይረስ ነጻ መሆናቸው መረጋገጡን ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አስታውቋል።

ፍርድ ቤቱ የተመለከተው ሌላው ጉዳይ፤ የእነ ጃዋር ጠበቆች ከደንበኞቻቸው ጋር በሚገናኙበት ስፍራ ካሜራ መገጠሙን በተመለከተ ባለፈው ችሎት ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ነው። ጠበቆች ካሜራው በፍርድ ቤት ትዛዝ ይነሳል ቢባልም ከደንበኞቻቸው ጋር አሁንም በሚስጥራዊ ቦታ መገናኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

“ካሜራው ሲነሳ ተደውሎ ትጠራላችሁ ተብለን ነበር። በእለቱ ግን 11 ሰዓት ሊሆን 10 ደቂቃ ሲቀር ነው የጠሩን፤ ሰዓት በቂ አልነበረም” ብለዋል። “በማግስቱ ሶስት ሰዓት ከሰላሳ እንድትመጡ ተብለን ብንሄድም፤ ‘መግባት አትችሉም’ ተብለን ተመልሰናል። ይህም ደንበኞቻችን አግኝተን ሂደቱን እንዲያውቁት ለማስረዳት እንዳንችል አድርጎናል” ብለዋል። “ይህ ሂደት በቅንነት ካልታየም ወደ ፊት መሄድ አንችልም” ሲሉም የእነ ጃዋር ጠበቆች አመልክተዋል። 

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ የተጠየቀው የፌደራል ፖሊስም፤ ተጠርጣሪ እና ጠበቃን ለማገናኘት ስራ ላይ እየዋለ ያለው አዳራሽ ቤተ መጽሐፍት እንደነበረ እና ካሜራዎቹም በውስጡ ያለውን ውድ መጽሐፍት ለመጠበቅ መሆኑን ገልጿል። “እንደሚታወቀው ቢሮአችን አዲስ ነው” ያለው ፖሊስ ካሜራውም በቦታው የነበረው በቀደመው አገልግሎቱ እንጂ ሆን ተብሎ አለመሆኑን ገልጿል። 

በዚህም መሰረት ሌላ አዲስ ክፍል ውስጥ እንዲነጋገሩ መመቻቸቱን እና ጠበቆችም ደንበኞቻቸውን ማናገራቸውን አስረድቷል። ለዚህም ሁሌም እንደሚደረገው ደንበኛ እና ጠበቃ የሚገናኙ ጊዜ የሚፈረም አጀንዳ መኖሩን እና ይህንንም ማስረጃ ማቅረብ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

ጠበቆቹ በበኩላቸው “በቂሊንጦም ሆነ በሌሎች እስር ቤቶች ደንበኞቻችንን አነጋግረን ስንወጣ እንጂ ስንገባ አንፈርምም። እዚህ ግን ስንገባ ነው የሚያስፈርሙን። ይህም አግባብ የለውም” ሲሉ ተከራክረዋል። ፖሊስ ማስረጃዬ የሚለው ይህንን መሆኑን እና ይህንን መቃወማቸውንም ጠበቆች አስረድተዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ጠበቆች ደንበኞቻቸውን ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ ሁኔታ የማግኘት መብት እንዳላቸው እና ይህንንም ፖሊስ እንዲፈጽም አዝዟል። ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝም “ፖሊስ የመፈጸም ግዴታ አለበት ይህንን ካልፈጸመ ፍርድ ቤቱ በህጉ መሰረት እርምጃ ይወስዳል” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል። 

ፍርድ ቤቱ አዲስ ትዕዛዞችን ካስተላለፈ በኋላ፤ አቃቤ ህግ በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ያቀረባቸውን ሁለት ምስክሮች ቃል በዝግ ችሎት አዳምጧል። ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት እና የተጠርጣሪዎችን እንዲሁም የአቃቤ ህግ አቤቱታዎችን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለመጪው ሰኞ፤ ነሐሴ 18፤ 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው ፍርድ ቤቱ በዚሁ የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)