በትግራይ ክልል ከሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ 45 በመቶው አሁንም ስራ አልጀመሩም ተባለ

በትግራይ ክልል ከሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ 45 በመቶው፤ ከጤና ጣቢያዎች ደግሞ 48 በመቶው እስካሁን ስራ አለመጀመራቸውን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ። ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በሽሬ ከተማ የተጠለሉ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ ቀደመ ቀያቸው ለመመለስ ኮሚቴ ማቋቋሙንም ገልጿል። 

የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ያስታወቀው ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 2 በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። በዛሬው መግለጫ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ እና የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያዎችን አቅርበዋል። 

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ በትግራይ ክልል የሚገኙ የጤና ተቋማት ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለጋዜጠኞች አብራርተዋል። “በአሁኑ ወቅት 55 በመቶ ሆስፒታሎች እና 52 በመቶ ጤና ጣቢያዎች ስራ እንዲጀምሩ ተደርገዋል” ብለዋል። ከእነዚህ የጤና ተቋማት ሰራተኞች ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ስራ ገበታቸው መመለሳቸውንም አብራርተዋል። 

“የተቀሩት የጤና ተቋማት የደረሰባቸውን ጉዳት የተመለከተ ምዘና ተሰርቷል። 14 ሆስፒታሎች እና 58 የጤና ማዕከሎችን ጠግኖ ሥራ ለማስጀመር በፌደራል መንግስት ገንዘብ ተመድቧል” ሲሉም ሚኒስትሯ አክለዋል።  

በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ለሚገኙ የክልሉ የጤና ተቋማት የህክምና ቁሳቁሶች እና መድሃኒቶች መሰራጨታቸውንም ዶ/ር ሊያ አስረድተዋል። የትግራይ ክልል የነበሩትን አብዛኞቹን አምቡላሶቹን ማጣቱን ለጋዜጠኞች የገለጹት የጤና ሚኒስትሯ፤ በክልሉ ጤና ቢሮ ስር በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ አምቡላንሶች 58 ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር 12 አምቡላንሶችን ለትግራይ ክልል መስጠቱን፤ የተለያዩ ክልሎች ደግሞ ስምንት አምቡላንሶችን ለክልሉ ማዋጣታቸውን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል። “ተጨማሪ አምቡላንሶች ከመንግስት እና ከአጋሮች ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው” ያሉት ዶ/ር ሊያ በአሁኑ ወቅት 65 አምቡላንሶች በጥገና ላይ እንዳሉም አስታውሰዋል።

በክልሉ ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆናቸው ህፃናት በተመጣጠነ ምግብ እጦት ተጠቅተው እንደሆነ ለመለየት፤ ባለፉት ሁለት ወራት በጤና ተቋማት እና ተንቀሳቃሽ ቡድኖች ምርመራ መደረጉን ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል። ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህጻናት ተደረገ በተባለው በዚህ ምርመራ “የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጦት የተገኘባቸው” 2,780 ህጻናት ብቻ ናቸው ተብሏል። ለእነዚህ ህጻናት አልሚ ምግብ መቅረቡን የጤና ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ዶ/ር ሊያ ከዚህም በተጨማሪ የጾታ ጥቃት ተጎጂዎች እና የኮቪድ 19ን ጉዳይ በመግለጫቸው አንስተዋል። የፆታ ጥቃት ለደረሰባቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች እገዛ ለማድረግ 57 የጤና ባለሙያዎች በስድስት ከተሞች ተሰማርተዋል ብለዋል። ከጤና ባለሙያዎቹ ውስጥ የአዕምሮ ጤናን ጉዳይ የሚከታተሉ እንዳሉበትም ጠቁመዋል። በትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየው የኮቪድ-19 ምራመራ መጀመሩንም አክለዋል። 

በዛሬው መግለጫ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በሽሬ ከተማ የተጠለሉ የክልሉ ነዋሪዎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታን የተመለከተው ይገኝበታል። የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለጋዜጠኞች እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት ዝናባማው ወቅት ከመጀመሩ በፊት በሽሬ እና ሌሎች የትግራይ መጠለያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ 40 አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረዋል። 

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሽነት እንደተቋቋመ በተነገረለት በዚህ ኮሚቴ ውስጥ፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ እና የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አገኘሁ ተሻገር ተካትተዋል። ስለ ተፈናቃዮቹ እጣ ፈንታ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ኮሚሽነር ምትኩ “ዕቅድ አዘጋጅተናል። ይኸን ዕቅድ በመጠቀም ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየሰራን ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። 

በትግራይ ጠኔ ተከስቷል?

በትግራይ ክልል “የከፋ ረሀብ ሊከሰት ይችላል” ለሚለው የዓለም አቀፍ ተቋማት ስጋት፤ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነሩ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ኮሚሽነር ምትኩ የመዝገበ ቃላት ሶስት መስፈርቶችን ጠቅሰው መንግስታቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊዎችን ጨምሮ በምዕራባውያኑ የሚወቀስበትን የጠኔ (famine) ጉዳይ አስተባብለዋል።

ጠኔ ተከስቷል ለማለት በአንድ አካባቢ ቢያንስ 20 በመቶ አባወራዎች የከፋ የምግብ እጥረት ሊገጥማቸው፤ ከ30 በመቶ በላይ ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሊገጥማቸው እንዲሁም ከአስር ሺህ ሰዎች መካከል በየቀኑ በረሀብ ምክንያት ሁለት ሞት መከሰት እንደሚኖርበት አብራርተዋል። “በአሁኑ ወቅት ሁሉም መረጃዎች የተሰራጩት 20 በመቶው የክልሉ ሕዝብ የምግብ እጥረት ገጥሞታል በሚለው የመጀመሪያው መመዘኛ ነው” ያሉት አቶ ምትኩ፤ ጠኔ ተከስቷል ከሚለው ድምዳሜ ለመድረስ ሶስቱ መመዘኛዎች አልተሟሉም የሚል ሙግት አቅርበዋል። 

“የምግብ እጥረት የለብንም። ምክንያቱም 91.3 በመቶ ተረጂዎች በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) በሚታገዙ አምስት የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ዕርዳታ ቀርቦላቸዋል” ሲሉም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚቀርበውን ወቀሳ ተከላክለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ረገድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁመራ፣ ዳንሻ እና ማይካድራን በመሳሰሉ የምዕራባዊ ትግራይ አካባቢዎች ብቻ የተወሰነ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

“ችግሩ በታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል የሚገኙ ተረጂዎችን እንዴት ዕርዳታ ማድረስ ይቻላል? የሚለው ነው። ምክንያቱም በተለያየ ቦታ የደፈጣ ጥቃት የፈጸሙ እና ተኩስ የከፈቱ የህወሓት ቅሪት ኃይሎች አሉ። ይኸ ነው ፈተናው”

አቶ ምትኩ ካሳ – የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች እና ሚሊሺያዎች የዕርዳታ ሥርጭት እንዲስተጓጎል አድርገዋል የሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ አሜሪካንን ጨምሮ ከምዕራባውያን አገራት እና ተቋማት ቢደመጥም፤ ኮሚሽነር ምትኩ ግን ለእዚህ ጉዳይ “የህወሓት ቅሪት ኃይሎች” ያሏቸውን ተጠያቂ አድርገዋል። አምስቱ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች “በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ተረጂዎችን ለማገዝ በቂ ሐብት አላቸው” የሚሉት ኮሚሽነሩ ችግሩ ሌላ ነው ባይ ናቸው። 

“ችግሩ በታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል የሚገኙ ተረጂዎችን እንዴት ዕርዳታ ማድረስ ይቻላል? የሚለው ነው። ምክንያቱም በተለያየ ቦታ የደፈጣ ጥቃት የፈጸሙ እና ተኩስ የከፈቱ የህወሓት ቅሪት ኃይሎች አሉ። ይኸ ነው ፈተናው። ሰራተኞቹን፣ ምግብ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎችን አጥቅተዋል” ሲሉም ለእርዳታ ስርጭት መስተጓጎል ተፈላሚውን ወገን ተጠያቂ አድርገዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት የእርዳታ ድርጅቶች ያለ ገደብ በትግራይ እንዲንቀሳቀሱ ማድረጉን በተደጋጋሚ ቢገልጽም፤ በምዕራባውያኑ ዘንድ ያለው ግፊት ግን እንደቀጠለ ነው። የUSAID አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ በሰጠበት በዛሬው ዕለት “የዕርዳታ እገዳን ለማስቆም እና ግጭቱን ለማብቃት በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር በርካታ ወሳኝ ስብሰባዎች” እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

“ከስድስት ሚሊዮን የትግራይ ክልል ነዋሪ፤ 5.2 ሚሊዮኑ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉበት አንገብጋቢ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። ኹከት በርትቷል። በታጣቂዎች የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር ተስፋፍቷል። ጠኔ እያንዣበበ ነው” ያሉት ሳምንታ ፓወር፤ ወቅታዊ የክልሉ ሁኔታ “ቀውስ” ሳይሆን “ጥፋት” እንደሆነ በትዊተር ባሰፈሩት ጠጠር ያለ መልዕክት ገልጸዋል።   

በትግራይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ በአፋጣኝ መፍትሔ ካልተፈለገለት ወደ ጠኔ ሊሸጋገር ይችላል የሚለው ስጋት ከአሜሪካ በተጨማሪ በተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ተቋማት ዘንድም በተደጋጋሚ እየተደመጠ ነው። በትግራይ እርዳታ ከሚያከፋፍሉ አምስት የግብረ ሰናይ ድርጅቶች አንዱ የሆነው የዓለም የምግብ ድርጅት 91 በመቶ የክልሉ ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ባለፈው ሳምንት አስታውቆ ነበር። 

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊ በትላንትናው ዕለት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “በትግራይ ሰዎች በረሀብ ምክንያት እየሞቱ ነው። ጊዜ እያለቀ ነው። የዕርዳታ አቅርቦቱን በመጨመር ጥፋትን ለማስቀረት ያልተገደበ የሰብዓዊ እንቅስቃሴ እንፈልጋለን” ሲሉ ሁሉም ወገኖች ቁርጠኛ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)