ምርጫ ቦርድ ለ54 የምርጫ ክልሎች የታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ችግር እንደነበረባቸው ገለጸ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ካሳተማቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ውስጥ ለ54 የምርጫ ክልሎች የታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ችግር እንደነበረባቸው ገለጸ። የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ ረቡዕ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት “የደረስንባቸው ትልልቅ ችግሮች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከችግሮቹ መካከል ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉ ዕጩዎች በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ታትመው መገኘታቸው አንዱ እንደሆነ የቦርዱ ሰብሳቢ ለውይይቱ ተሳታፊዎች አስረድተዋል። በዕጩነት የተመዘገቡ ተወዳዳሪዎች ያልተካተቱባቸው የታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችም ቦርዱ ከመረጃ ቋቱ ጋር ባደረገው የማመሳከር ሂደት ወቅት መገኘታቸውን አስረድተዋል። በፓርቲዎች የተቀየሩ ዕጩዎች በታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ሰፍረው መገኘታቸውንም እንዲሁ ሰብሳቢዋ በችግርነት አንስተዋል።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ምርጫ ቦርድ በጽምጽ መስጫ ወረቀቶቹ ላይ ችግር እንዳለባቸው ያወቀው ከሁለት ቀን በፊት ግንቦት 30 ባካሄደው የሰነድ ማመሳከር እንደሆነ የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ቦርዱ ማምሻውን ባወጣው የምርጫ ክልሎች ዝርዝር መሰረት፤ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት ችግር ያልተስዋለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ፣ የሲዳማ እና ሀረሪ ክልሎች ናቸው።

ችግሩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው 54 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት በደቡብ እና ሶማሌ ክልሎች የሚገኙ መሆኑን የምርጫ ቦርድ መግለጫ አሳይቷል። ከሁለቱ በመቀጠል በርከት ያሉ የምርጫ ክልሎቹ በችግሩ ተጽዕኖ የደረሱበት የአማራ ክልል ነው። አፋር፣ ጋምቤላ እና ኦሮሚያ በተከታይነት ሲቀመጡ የድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በአንድ የምርጫ ክልሉ ላይ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ችግር ተገኝቶበታል።    

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ “የተፈጠረው ስህተት መስሪያ ቤቱ ኃላፊነት የሚወስድበት ስህተት ነው። እኔም የተቋሙ መሪ ኃላፊነት እወስዳለሁ” ሲሉ በመስሪያ ቤታቸው ለተፈጠረው ችግር ይፋዊ ይቅርታ ጠይቀዋል። የችግሩ መንስኤ “ማሻሻያዎችን በትክክል ተረድተው መፈጸም የሚችሉ ባለሙያዎች እጥረት” ነው ሲሉም ለተሰብሳቢዎቹ ገልጸዋል። 

በዘንድሮው ምርጫ የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ በምርጫ አስፈጻሚዎች ፊት በአካል በመቅረብ እና በበይነ መረብ አማካኝነት መከናወኑን የገለጹት ብርቱካን፤ ይህ አካሄድም ከዚህ ቀደም ያልነበረ እና ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት መሰል ምዝገባ ይካሄድ የነበረው በምርጫ ክልል ደረጃ ብቻ እንደነበርም አስታውሰዋል።

የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን እገዛን የሚጠይቁ እኒህን መሰል ማሻሻያዎችን በቅጡ ተረድተው የሚተገብሩ ባለሙያዎች በብዛት አለመኖራቸው ቦርዱ ላጋጠመው ችግር አንዱ ምክንያት መሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል። የችግሩ መፈጠር ከእውቀት ወይም ከልምድ ማነስ ሊሻገር እንደሚችልም ብርቱካን በንግግራቸው  ጥቆማ ሰጥተዋል። ሰብሳቢዋ “ሆን ተብሎ የቦርዱን ስራ ለማስተጓል የተሰራ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለ” ሲሉ በአዲስ አበባው ራዲሰን ብሉ ለተሰበሰቡ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተናግረዋል።  

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ምርጫ ቦርድ ከድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው ችግር “በጣም ትልቅ የሆነ ቸልተኝነት አሳይተዋል” ባላቸው ሰራተኞች ላይ የማሰናበት እርምጃ መውሰዱን በዛሬው ስብሰባ ቢገልጽም፤ ብዛታቸውንም ሆነ ማንነታቸውን ከመግለጽ ግን ተቆጥቧል። ምርጫ ቦርድ የህትመት ችግር በተፈጠረባቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ምክንያት የእቅድ መስተጓጎል ቢገጥመውም፤ የድምጽ መስጫዎቹን እንደገና ለማሳተም ግን ተጨማሪ በጀት እንደማያስወጣው ተነግሯል። 

“ቦርዱ ያለው ጊዜ ውስን ነው” ያሉት ብርቱካን፤ ከድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት ችግር ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን እክል ለመቅረፍ ሁለት አማራጮችን  እንዳቀረበ ተናግረዋል። አንደኛው አማራጭ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን በሀገር ውስጥ ማሳተም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የህትመት ችግር በተከሰተባቸው የምርጫ ክልሎች ሊካሄድ የነበረውን ምርጫ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ደምሮ ማካሄድ ነው። 

ምርጫ ቦርድ በጸጥታ ችግር እና በሌሎችም ምክንያቶች የመራጮች ምዝገባ ተስተጓጉሎባቸዋል ባላቸው 40 የምርጫ ክልሎች፤ ሰኔ 14 የድምጽ መስጠት ሂደት እንደማያከናውን መግለጹ ይታወሳል። የቦርዱ አንደኛው አማራጭ፤ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት ችግር የተስተዋለባቸውን 54 የምርጫ ክልሎች ከ40ዎቹ ጋር በመደመር፤ ምርጫውን በተለየ የጊዜ ሰሌዳ፣ በአንድ ላይ ማካሄድ ነው። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

በዛሬው ስብሰባ ላይ ከተካፈሉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ውስጥ በአብዛኞቹ የተደገፈው አማራጭ፤ በድጋሚ የሚታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት በሀገር ውስጥ ማካሄድ  ነው። የድጋሚ ህትመቱ ምስጢራዊነቱን ጠብቆ በመንግስታዊው ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት እንዲከናወን ገዢው ፓርቲን ጨምሮ በሶስት ፓርቲዎች ምክረ ሀሳብ ቀርቧል። 

የሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ደግሞ የድጋሚ ህትመቱ በውጭ ሀገር ተከናውኖ ምርጫው ለተወሰኑ ቀናት እንዲራዘም ጠይቀዋል። የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲን በመወከል በስብሰባው ላይ የተገኙ ተሳታፊ በበኩላቸው በሶማሌ ክልል ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ሙሉ በሙሉ በሌላ ጊዜ እንዲካሄድ አሳስበዋል።  የሶማሌ ክልል ምርጫ፤ በተለየ የጊዜ ሰሌዳ ምርጫውን ከሚያከናውኑ የምርጫ ክልሎች ጋር በአንድ ላይ እንዲካሄድ ያላቸውን አቋም አንጸባርቀዋል። 

“ሰኔ 14 ምርጫ እናደርጋለን። ምንም ጥርጥር የለውም”

ብርቱካን ሚደቅሳ – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ

ከፓርቲ ተወካዮች የተነሱትን ሃሳቦች እና ጥያቄዎች ያደመጡት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ ፈርጠም ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። “ሰኔ 14 ምርጫ እናደርጋለን። ምንም ጥርጥር የለውም” ሲሉ ምርጫው በድጋሚ እንደማይራዘም አስታውቀዋል።

የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን በብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ማሳተምን በተመለከተ ደግሞ ስራው ሂደቱ የሰው ኃይል ጭምርን የሚያካትት መሆኑን በተግዳሮትነት ጠቅሰዋል። “ብርሃን እና ሰላም የሚቆጥሩት በሰው ኃይል ነው” ያሉት ብርቱካን፤ ይህ አሰራር ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል። ቦርዱ ይህን በተመለከተ በውጭ ሀገር ካሉት የድምጽ መስጫ ወረቀት አታሚዎች ጋር ተመካክሮ፤ በነገው ዕለት የመጨረሻ ውሳኔውን ያሳውቃል ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)