እነ ጃዋር መሐመድ ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀሩ

በሃሚድ አወል

በአቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የተከሰሱ ተከሳሾች፤ ጉዳያቸውን እየተመለከተ በሚገኘው ችሎት ፊት ለሶስተኛ ጊዜ ሳይቀርቡ ቀሩ። ተከሳሾቹ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 29፤ 2013 በጠበቆቻቸው በኩል ለችሎቱ ባቀረቡት የጹሁፍ ማመልከቻ ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ በድጋሚ አስታውቀዋል። 

ተከሳሾቹ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ጸረ-ሽብርና ህገ መንግስታዊ ወንጀል ችሎት ሰኔ 21 ፤ 2013 ባስገቡት ማመልከቻ፤ ችሎት ላይ መገኘት ስለማይችሉበት ምክንያት በተመሳሳይ ሁኔታ መግለጻቸው ይታወሳል። በዛሬው ማመልከቻቸው ደግሞ “ክርክሩ የፖለቲካ ክርክር ነው። የሚፈታውም በአስፈፃሚው አካል እንጂ በፍርድ ቤቱ አይደለም’’ ማለታቸውን የተከሳሾችን ደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ጠበቃ ቱሊ ባይሳ ተናግረዋል።

ጠበቃ ቱሊ፤ ተከሳሾች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ከአንዴም ሁለት ጊዜ እንዳነጋገሯቸው ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። ሆኖም ተከሳሾቹ “ፍርድ ቤቱ የስርዓቱ አካል ስለሆነ፤ ፍርድ ቤት መቅረብ አንፈልግም” ማለታቸውን ጨምረው አስረድተዋል። እነ አቶ ጃዋር ባለፈው ሳምንት በጻፉት ማመልከቻም ከዚህ በኋላ በችሎት ላይ የማይገኙት “ በፍትህ ላይ በሚተወን ድራማ ላይ ተሳታፊ ላለመሆን” ከውሳኔ ላይ በመድረሳቸው መሆኑን አስታውቀው ነበር። 

ተከሳሾቹ ዛሬ እና ባለፈው ሳምንት ችሎት ፊት ያልቀረቡት በራሳቸው ውሳኔ ቢሆንም፤ በሰኔ 10፤ 2013 በነበረው ቀጠሮ ግን ችሎት ያልተገኙት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነበር። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የወሰነው ከምርጫው ጋር በተያያዘ ባለ የጸጥታ ስጋት ምክንያት እንደነበር መግለጹ አይዘነጋም።  

የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎው የተከሳሾችን የፍርድ ቤት አንቀርብም ማመልከቻ ለሁለተኛ ጊዜ ቢያደምጥም፤ ቀጣይ ክርክር ለማድረግ ተለዋጭ ቀጠሮ ከመስጠት ወደ ኋላ አላለም። በዚህም መሰረት ዐቃቤ ህግ በእነ ጃዋር ላይ የቆጠራቸው ምስክሮች ያለባቸውን የደህንነት ስጋቶች በተመለከተ ክርክር ለማድረግ ለሐምሌ 21፤ 2013 ቀጠሮ ሰጥቷል። በቀጠሮው ቀን ተከሳሾች እንዲቀርቡም ትዕዛዝ አስተላልፏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)