በእስር ላይ በሚገኙ 16 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

በተስፋለም ወልደየስ 

የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት በእስር ላይ በሚገኙ  16 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች ላይ ከሰባት እስከ 10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ዛሬ ፈቀደ። ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮውን የፈቀደው፤ የፌደራል ፖሊስ ምርመራዬን አልጨረስኩም በማለቱ ነው። 

በአፋር ክልል በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ የሚገኘው ይኸው ፍርድ ቤት ለዛሬ ቀጥሮ የነበረው፤ በሁለት የተለያዩ የፍርድ ቤት ውሎዎች የምርመራ ቀናት ተፈቅዶለት የነበረው የፌደራል ፖሊስ ያከናወናቸውን የምርመራ ተግባራት አድምጦ ውሳኔ ለማሳለፍ ነበር። ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 26፤ 2013 በዋለው ችሎት፤ በሶስት ምድቦች ተከፍለው በቀረቡ 16 ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ ሲያጣራቸው የቆያቸውን ምርመራዎች እና ቀሩኝ የሚላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አስረድቷል።

የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ የተመለከተው የሁለት ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ነበር። በመቀጠልም የአውሎ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በቃሉ አላምረው፣ የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኛ አበበ ባዩ እና የቀድሞው የሰንደቅ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ፋኑኤል ክንፉ የተካተቱበት የሰባት ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ታይቷል። ፍርድ ቤቱ በስተመጨረሻ የተመለከተው የኢትዮ ፎረም አዘጋጅ ያየሰው ሽመልስ፣ የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞች የሆኑት ፋና ነጋሽ እና ምህረት ገብረክስቶስ ያሉበትን የሰባት ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ነው።

የሚወክሏቸው ጠበቆች በሌሉበት ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት አስራ ስድስቱ ተጠርጣሪዎች፤ በፖሊስ የምርመራ ሂደት ላይ የየራሳቸውን ጥያቄ በማንሳት ተከራክረዋል። አራት ሰዓት ተኩል ገደማ በፈጀው በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ተጠርጣሪዎቹ ወደ አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ከተዘዋወሩ በኋላ ያጋጠማቸውን እና የደረሰባቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። 

የጋዜጠኞቹን ሁኔታ ለመከታተል በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በሚገኘው ፍርድ ቤት ተገኝቶ የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ የዕለቱን የችሎት ውሎ ለመከታተል ለፍርድ ቤት ጥያቄ ቢያቀርብም፤ መርማሪ ፖሊስ ተቃውሞ በማቅረቡ ጋዜጠኞቹ እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞቹ ያቀረቧቸውን ክርክሮች እና አቤቱታዎች ማድመጥ ሳይችል ቀርቷል። ጋዜጠኞቹ እና ሰራተኞቹ፤ ክርክሮቻቸውን እና አቤቱታቸውን በስሜት ተውጠው፣ በከፍተኛ ድምጽ ያቀርቡ ስለነበር፤ ዘጋቢውን ጨምሮ ከችሎቱ ውጭ በአቅራቢያው የነበሩ ግለሰቦች ጥቅል ሀሳቡን መረዳት ችለዋል።

አስራ ስድስቱ ተጠርጣሪዎች “ለፖሊስ እስካሁን የተሰጠው የምርመራ ጊዜ በቂ ስለሆነ በነጻ ልንለቀቅ ይገባል” የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ ተደምጠዋል። ፍርድ ቤቱ ይህን የማይቀበል ከሆነ ደግሞ የዋስትና መብታቸው ይከበርላቸው ዘንድ አሳስበዋል። በሁሉም ተጠርጣሪዎች የተነሳው ሌላው ጉዳይ ከቤተሰብ ጋር መገናኘት ያለመቻላቸው ሁኔታ ነው። 

ተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦቻቸው የታሰሩበትን ቦታ ባለማወቃቸው፤ ላለፉት 35 ቀናት ያለ ቅያሬ ልብስ በችግር ላይ እንዳሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ይህ ሁኔታ በተለይ በሴት ተጠርጣሪዎች ላይ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉን በምሬት ተናግረዋል። ተጠርጣሪ ሴቶች ችግሮቻቸውን ከእንባቸው ጋር እየታገሉ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ፤ ከችሎት ውጭ ሆነው ጉዳዩን ሲያደምጡ የነበሩ ሴቶች ሲያለቅሱ ታይተዋል። 

በአዋሽ ሰባት ኪሎ በእስር ላይ ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች መካከል አራቱ ሴቶች ናቸው። ፋና ነጋሽ፣ ምህረት ገብረክርስቶስ፣ ፍቅርተ የኑስ እና ዊንታና በርሄ የተባሉት እነኚህ ተጠርጣሪዎች በአውሎ ሚዲያ በጋዜጠኝነት፣ በግራፊክስ ኤዲተንግ ባለሙያነት እና በሰው ሃይል አስተዳደር ክፍል የሚሰሩ እንደነበሩ ጉዳያቸውን የያዙት ጠበቃ አቶ ታደለ ገብረመድህን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

አስራ አንድ የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞች እና ሰራተኞችን እንዲሁም ሁለቱን የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞች የሚወክሉት ጠበቃ ታደለ፤ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት “አካልን ነጻ የማውጣት” (habeas corpus) ክስ እስኪመሰርቱ ድረስ ለአንድ ወር ገደማ ያህል የተጠርጣሪዎቹ ደብዛ ጠፍቶ ነበር። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ የፍትሃ ብሔር ችሎት የቀረበለትን “አካልን ነጻ የማውጣት” ክስ መመልከት ከጀመረ በኋላ ግን፤ የፌደራል ፖሊስ ባጋጠመው የቦታ እጥረት ምክንያት ተጠርጣሪዎቹን ወደ አዋሽ ሰባት ኪሎ ማዛወሩን ገልጿል።  

ተጠርጣሪዎቹ በአዋሽ ሰባት ኪሎ ምርመራ እየተካሄደባቸው ያለው በፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው መሆኑን ፖሊስ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መግለጹ ይታወሳል። ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀው “ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ወንጀል ነው።

የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት፤ የፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት በእርግጥም በተጠርጣሪዎቹ ላይ የምርመራ ጊዜ መፍቀዱን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲቀርብ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት፤ ፖሊስ ፍቃዱ መሰጠቱን የሚያመለክት የፍርድ ቤት ደብዳቤ ባለፈው ሐሙስ 22 በነበረ የችሎት ውሎ ላይ አቅርቧል። ሆኖም የተጠርጣሪዎች ጠበቃ፤ ከደብዳቤው በተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ተያይዞ መቅረብ ነበረበት በሚል ተከራክረዋል። 

ጠበቃው በሰነዱ ላይ የተጠቀሰው ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት የቀረቡበት ቀን ላይም ጥያቄ አንስቷል። ፖሊስ ለጠበቃው መከራከሪያ ምላሽ ቢሰጥም፤ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ግን የፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት የተጠርጣሪዎችን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ እየተመለከተ ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

ለመጪው ሐሙስ ሐምሌ 29 ተጨማሪ ማስረጃ እንዲያቀርብ የታዘዘው የአዋሽ ፈንታሌ ፍርድ ቤት በበኩሉ፤ በዛሬው ውሎው በአስራ ስድስቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ለሶስተኛ ጊዜው የጊዜ ቀጠሮ መፍቀዱን አስታውቋል። ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ምድብ በቀረቡት ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ እስከ ነሐሴ 6፤ 2013 ምርመራ እንዲያካሄድ ፍቃድ ሰጥቷል። 

አራት ሴት ተጠርጣሪዎች እና ጋዜጠኛ ያየሰው  ሽመልስ የተካተቱበት የቀሪ የሰባት ተጠርጣሪዎች ምርመራ ደግሞ በሰባት ቀናት ውስጥ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። ሰዓታትን የፈጀው የዛሬው የችሎት ውሎ የተጠናቀቀው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)