በሃሚድ አወል
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ የተከሰሱ 21 ተከሳሾች ያቀረቡት ዋስትና ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ለከነገ ወዲያ ሐሙስ ነሐሴ 13 ቀጠሮ ሰጠ። ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተቃውሟል።
ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 11፤ 2013 የተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር እና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ በጠበቆች በኩል በጽሁፍ የቀረበው የተከሳሾች የዋስትና ጥያቄ ላይ ግራ ቀኙን አከራክሯል። የዋስትና ጥያቄው ግልባጭ በችሎት ፊት የደረሰው ዐቃቤ ህግ፤ ተከሳሾች የጠየቁት የዋስትና መብት በሁለት ምክንያቶች ተቀባይነት እንዳይኖረው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ዐቃቤ ህግ የተከሳሾችን የዋስትና መብት ለመቃወም ያቀረበው የመጀመሪያ ምክንያት፤ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 21 ተከሳሾች ውስጥ ሃያዎቹ ክስ የቀረበባቸው “የሽብር ወንጀል ነው” የሚል ነው። ከ59ኛ ተከሳሽ ውጭ ያሉት ተከሳሾች በተደራራቢ ወንጀሎች የተከሰሱ መሆናቸውን ዐቃቤ ህግ በመከራከሪያነት አንስቷል።
በተከሳሾች ተፈጸመ በተባለው ወንጀል ምክንያት “ለሀገር ደህንነት ሲባል በቁጥር የማይጠቀስ የሰው ህይወት ማለፉን” በተጨማሪነት የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ፤ ሁለቱም ክሶች ከዕድሜ ልክ እስከ ሞት የሚያስቀጡ መሆናቸው “ተከሳሾችን ዋስትና ያስከለክላቸዋል” ሲል ተከራክሯል። ተከሳሾች ባቀረቡት መከራከሪያ “ጦርነት አለ፤ ሞቱም የተከሰተው በጦርነቱ ነው” ማለታቸውን ያነሳው ዐቃቤ ህግ፤ ሆኖም በእነርሱ ላይ የቀረበባቸው ክስ የሽብር እንጂ የጦር ክስ አለመሆኑን አስረድቷል። “ለዚህ ሁሉ ጥፋት ምክንያት የሆነው፤ [ተከሳሾች] የአገሪቱን መንግስት በመሳሪያ ኃይል ለመለወጥ በመሞከራቸው ነው” ሲልም አክሏል።
ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀል በ2011 ተጀምሮ በጥቅምት 24፤ 2013 የተፈጸመ ነው ያለው ዐቃቤ ህግ፤ ከጥቅምት 4 እስከ ህዳር መጀመሪያ ያሉት ጊዜያቶች “የጦርነት ወቅቶች አይደሉም” ሲል ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል። ዐቃቤ ህግ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ መደረግን በተመለከተ ያቀረበው መከራከሪያ፤ አንድ ክስ ብቻ የቀረበባቸው 59ኛ ተከሳሽ አቶ ዶሪ አስገዶምን ጭምር የሚመለከት እንደሆነም አመልክቷል።
የአሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዶሪ የተከሰሱት “በኢ-ህገመንግስታዊ ምርጫ ተሳትፈዋል” በሚል ነው። ተከሳሹ በህገ እውቅና አግኝቶ የተቋቋመን መንግስታዊ አስተዳደርን የመቀየር ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ተከስሰዋል። ዐቃቤ ህግ ተከሳሹ “የቀረበባቸው ክስ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስቀጣ ነው” በማለት ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ እንዲያደርገው ጠይቋል።
ተከሳሹ የመኖሪያ አድራሻቸው መቐለ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው ዐቃቤ ህግ፤ “ከፍተኛ” የተባለውን ቅጣት ፍራቻ፣ በዋስትና ከተፈቱ በኋላ “ችሎት ፊት ተመልሰው” ይቀርባሉ የሚል እምነት እንደሌለው አስታውቋል። አቶ ዶሪ፤ “በቀዳሚ ምርመራ የተሰሙባቸውን ምስክሮች ማንነት ያውቃሉ ስለሆነም በዋስትና ቢወጡ በምስክሮች ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ” ሲልም ዐቃቤ ህግ ስጋቱን ገልጿል።
ለዐቃቤ ህግ የመልስ መልስ የሰጡት የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ደንበኞቻቸው በሁለተኛው ክስ ከተከሰሱበት የህግ ድንጋጌ ጀምሮ ተቃውሞ አቅርበዋል። ዐቃቤ ህግ “የወንጀሉ ጅማሮ 2011 ነው” ማለቱን በተመለከተ፤ ወንጀሉ ተፈጸመ በተባለበት ወቅት “ተከሳሾች የተከሰሱበት የህግ ድንጋጌ አልነበረም። ህጉ ወደ ኋላ ሄዶ ተግባራዊ ሊሆን አይገባም” በማለት ተከራክረዋል።
የክሱን አይነት በተመለከም ዐቃቤ ህግ በክስ ቻርጁ ላይ ከ20 ጊዜ በላይ “ጦርነት የሚለውን ቃል ተጠቅሟል” ሲሉ ደንበኞቻቸው የተከሰሱበት “የሽብር ህግ ተፈጻሚ መሆን አይገባውም” ብለዋል። ተከሳሾች ነጻ ሆነው የመገመት መብት እያላቸው በምስክሮች ላይ ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ መባሉም አግባብ አይደለም ሲሉም ጠበቆቹ ተቃውመዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የከፍተኛው ፍርድ ቤት፤ በዋስትና ጥያቄው ላይ በጽህፈት ቤት በኩል ብይን ለመስጠት ለሐሙስ ነሐሴ 13፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የዋስትና ጥያቄ ከማስተናገዱ በፊት፤ ለዛሬ አሳድሮት የነበረውን የክስ ንባብ አከናውኗል።
በሃምሳ ገጾች የተዘጋጀው የክስ ሰነድ፤ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በ58 ግለሰቦች እና አራት ድርጅቶች ላይ የመሰረተውን ክስ በዝርዝር አስቀምጧል። የመጀመሪያው ክስ የቀረበው የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ደብረጽዮን እና ምክትላቸው ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔርን (ሞንጆሪኖ) ጨምሮ በ42 ተከሳሾች ላይ ነው።
በዚህ ክስ ተከሳሾቹ ላይ የተጠቀሰባቸው ወንጀል፤ “በኃይል፣ በዛቻ፤ በአድማ እና ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ኢ-ህገመንግስታዊ ምርጫ በማካሄድ በሕገ መንግስት የተቋቋመን የክልል መንግስትን ለውጠዋል” የሚል ነው። ተከሳሾቹ በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ከተገኙ ከዕድሜ ልክ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
በመጀመሪያው ክስ የተካተቱት ሁለቱን የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ በ52 ተከሳሾች ላይ የቀረበው ሁለተኛው ክስ ደግሞ፤ የፌደራል መንግስትን በኃይል ለመለወጥ በማሰብ “በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት አድርሰዋል” የሚል ነው። ተከሳሾቹ ከ2011 ጀምሮ የፌደራል መንግስትን በመሳሪያ ጥቃት መለወጥ የሚችል የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ የተባለ የጦር ኃይል በማደራጀት ጥቃቱን መፈጸማቸውንም በክስ ሰነዱ ተብራርቷል።
ከ62ቱ ተከሳሾች ውስጥ፤ በሁለቱም ወንጀሎች ክስ የቀረበባቸው 32 ግለሰቦች ናቸው። በሁለቱም ክሶች ከተከሰሱት ውስጥ የህወሓት የስራ አስፈጻሚ አባላት የሆኑት ጌታቸው ረዳ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ዶ/ር አብረሃም ተከስተ፣ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ፣ ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂም እና አቶ ዓለም ገብረዋህድ ይገኙበታል፡፡ ከተከሳሾቹ ውስጥ ሃያ አንዱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ጉዳያቸው የሚታየው በሌሉበት ነው። በዛሬው የችሎት ውሎ በማረሚያ ቤት የሚገኙት ሃያ አንዱም ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀርበው ክሳቸው ተነብቦላቸዋል።
ፍርድ ቤቱ የዛሬ ውሎውን ከማጠናቀቁ በፊት ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ለጥቅምት 22፤ 2014 ቀጠሮ ሰጥቷል። በተጨማሪም የፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ላልዋሉ ቀሪ ተከሳሾች መጥሪያ እንዲያደርስ በድጋሚ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
የፌደራል ፖሊስ ሐምሌ 26፤ 2013 በዋለው ችሎት፤ በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ መጥሪያ ማድረስ አለመቻሉን አስታውቆ ነበር። ዐቃቤ ህግ በዛሬው ችሎት፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ በጋራ መጥሪያውን እንዲያደርሱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲያስተላልፍ ጠይቋል።
“የፌደራል ፖሊስ በየትኛውም ቦታ ገብቶ ተከሳሾችን የመያዝ ስልጣን አለው” ያለው ፍርድ ቤቱ፤ ትዕዛዙን ለፌደራል ፖሊስ ብቻ እንደሚጽፍ ገልጿል። ፍርድ ቤቱ፤ “የፌደራል ፖሊስ ከፈለገ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ድጋፍ መጠየቅ ይችላል” ብሏል። በዚሁ መዝገብ የተከሰሱ አራት ድርጅቶችን በተመለከተ ለህጋዊ ወኪሎቻቸው መጥሪያ እንዲደርሳቸው አዝዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)