በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በእስር ላይ የቆዩ አራት ጋዜጠኞች በዋስትና ተፈቱ

በተስፋለም ወልደየስ    

በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ለ49 ቀናት በእስር ላይ የቆዩት አራት የኢትዮ ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞች በዋስትና ተፈቱ። በዛሬው ዕለት ከእስር የተለቀቁት ጋዜጠኞች የ“ኢትዮ ፎረም” አዘጋጁ ያየሰው ሽመልስ እና ባልደረባው አበበ ባዩ፣ የአውሎ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በቃሉ አላምረው እንዲሁም በሚዲያው በተንታኝነት ይሳተፍ የነበረው ፋኑኤል ክንፉ ናቸው። 

የአራቱን ጋዜጠኞች የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት፤ እያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች አምስት ሺህ ብር ዋስትና አስይዘው እንዲፈቱ ውሳኔ አሳልፎ የነበረው ከትላንት በስቲያ ሰኞ ነሐሴ 10 በዋለው ችሎት ነበር። የጋዜጠኞቹ ቤተሰቦች ለዋስትና የተጠየቀውን ገንዘብ የዚያኑ ዕለት ከፍለው ቢያጠናቅቁም፤ ተጠርጣሪዎቹ ላለፉት ሁለት ቀናት ሳይፈቱ ቆይተዋል። 

ሆኖም ዛሬ፤ ረቡዕ ነሐሴ 12፤ ጠዋት ሁለት ሰዓት ገደማ፤ አራቱን ጋዜጠኞች ጨምሮ ስምንት ተጠርጣሪዎች በእስር ከቆዩበት የአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ መፈታታቸውን የቀድሞው የ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ፋኑኤል ክንፉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከእስር የተለቀቁት ጋዜጠኞች ከረፋዱ አምስት ተኩል ገደማ አዲስ አበባ መግባታቸውንም ገልጿል። 

ከጋዜጠኞቹ ጋር በአንድ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ተካትቶ ፍርድ ቤት ሲቀርብ የቆየው አክቲቪስት ጸጋዘአብ ኪዳኔ፤ ተመሳሳይ የዋስትና ገንዘብ በማስያዝ መፈታቱንም ፋኑኤል አስረድቷል። ከጋዜጠኞቹ ጋር አብረው ከተፈቱት ሌሎች ተጠርጣሪዎች ውስጥ የባይቶና ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክብሮም በርሄ እና የፈንቅል እንቅስቃሴ አባል የሆነው አቶ ገብረሚካኤል ተስፋዬ ይገኙበታል። በዋስትና ከተፈቱት ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ጋር ካሱ አዲስ የተባለ ሌላ አክቲቪስትም በዛሬው ዕለት ከእስር ተለቅቋል። 

ዛሬ በዋስትና ከተፈቱት ጋዜጠኞች ጋር በአንድ ላይ በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩ 16 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች መካከል አስሩ ባለፈው ነሐሴ 3፤ 2013 ከእስር መፈታታቸው አይዘነጋም። በቃሉ አላምረው እና ፋኑኤል ክንፉን ጨምሮ አስራ ሁለት የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰኔ 22፤ 2013 ነበር። የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞቹ አበበ ባዩ እና ያየሰው ሽመልስ ደግሞ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰኔ 24 እና 25፤ 2013 ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)