የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሊያወያይ ነው

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፓለቲካ ፓርቲዎችን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ነገ ቅዳሜ ነሐሴ 29፤ 2013 ሊያወያይ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይቱ እንዲሳተፉ ጥሪ የደረሳቸው በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ነው ተብሏል። 

በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል ነገ ከጠዋቱ 2 ሰዓት 30 ጀምሮ በሚካሔደው ውይይት ላይ ሀገር አቀፍ እና የክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶ/ር ራሄል ባፌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በውይይቱ ላይ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል። 

በነገው ስብሰባ ከእያንዳንዱ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ አራት፤ ከክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ሁለት አመራሮች እንደሚሳተፉ ጥሪው የደረሳቸው ሶስት ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። የስብሰባው ግብዣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መረጃዎችን በሚለዋወጡበት “የቴሌግራም ግሩፕ” ዛሬ አርብ ጠዋት እንደደረሳቸውም ጠቁመዋል። 

በውይይቱ እንዲሳተፉ የተጋበዙ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር፤ “የስብሰባው አጀንዳ ‘ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ’ ይበል እንጂ የትኛው ሀገራዊ ጉዳይ አንደሆነ አልተገለጸም” ብለዋል። የነገውን የስብሰባ አጀንዳ በተመለከተ የተጠየቁት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ፤ ውይይቱን ያዘጋጀው የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በመሆኑ ዝርዝር መረጃ የለኝም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። (በሃሚድ አወል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)