መስከረም 20 በሚከናወነው ምርጫ፤ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ ተባለ

በሃሚድ አወል

በሶስት ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከአስር ቀናት በኋላ በሚከናወነው ምርጫ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚወዳደሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ። ቦርዱ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሶማሌ ክልል ከሚካሄደው ምርጫ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ማግለላቸው፤ በምርጫው ሂደት ላይ “ተጽዕኖ አያሳድርም” ብሏል።

የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ በአዲስ አበባው ስካይላይት ሆቴል ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በሶማሌ በደቡብ እና ሐረሪ ክልሎች ላሉ 47 የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ለሚደረገው ምርጫ 210 ዕጩዎች በተወዳዳሪነት ቀርበዋል። በሶስቱ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ላሉ 378 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች 1,236 ዕጩዎች ለመመረጥ እንደሚወዳደሩም ኃላፊዋ ተናግረዋል።  

በመጪው መስከረም 20 ምርጫ ከሚከናወንባቸው የፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት በሶማሌ እና በደቡብ ክልል የሚገኙት ናቸው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች ውስጥ ባለፈው ሰኔ 14 ምርጫ የተካሄደባቸው በ436ቱ ላይ ብቻ ነው። በወቅቱ ሙሉ ለሙሉ ምርጫ ያልተካሄደበት የሶማሌ ክልል በፓርላማ 23 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፤ በመስከረም ሃያው ምርጫ በሁሉም ላይ ምርጫ ይደረጋል ተብሏል። 

ከእነዚህ የፓርላማ መቀመጫዎች በተጨማሪ ለ273ቱም የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች በዕለቱ ምርጫ እንደሚከናወን ተገልጿል። በዚህ ምርጫ ገዢው ብልጽግናን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎች ይወዳደራሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ ሶስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን አስታውቀዋል። 

በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎቻቸው በኩል በክልሉ በሚካሔደው ምርጫ ላለመሳተፍ የወሰኑት ፓርቲዎች ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ናቸው። ፓርቲዎቹ ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉት ከምራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ ላቀረቧቸው አቤቱታዎች ምርጫ ቦርድ “ተገቢውን ምላሽ አልሰጠም” በሚል ነው።  

የፓርቲዎቹን ውሳኔ ተከትሎ በሶማሌ ክልል ገዢውን ፓርቲ ለመፎካከር የቀረበው ብቸኛ ተቃዋሚ፤ የምዕራብ ሶማሌ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሆኗል። ተቃዋሚ ፓርቲው በመጪው ምርጫ እንደሚሳተፍ ሊቀመንበሩ አቶ ሂርሲ ዶል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የምዕራብ ሶማሌ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ለአንድ የፓርላማ እና ለ14 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች እንደሚወዳደር ከምርጫ ቦርድ የተገኘ መረጃ ያሳያል። 

የሶስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን ማግለል በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ፤ የፓርቲዎቹ ውሳኔ በምርጫ ሂደቱ ላይ “የሚያሳድረው ተጽዕኖ የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የፓርቲዎቹን ውሳኔ ተከትሎ ቦርዱ “ምንም የሚቀይረው ነገር” አለመኖሩንም ገልጸዋል። 

በመስከረም 20 በሚደረገው ምርጫ፤ እንደ ሶማሌ ክልል ሁሉ በበርካታ ቦታዎች ለፓርላማ መቀመጫዎች ምርጫ የሚደረገው በደቡብ ክልል ነው። የደቡብ ክልል ካለው 104 የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ውስጥ በአሁኑ ምርጫ ለውድድር የቀረቡት ሃያ ሁለቱ ናቸው። በፍርድ ቤት በነበረ ክርክር ምክንያት ሰኔ 14 ምርጫ ባልተከናወነበት በሐረሪ ክልልም፤ ለሁለት የፓርላማ መቀመጫዎች በዚሁ ዕለት ምርጫ ይደረጋል።

ለመጪው ምርጫ 7.6 ሚሊዮን ዜጎች ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውን በዛሬው የምርጫ ቦርድ መግለጫ ላይ ይፋ ተደርጓል። ከተመዘገቡት መራጮች ውስጥ 5.1 ሚሊዮን የሚሆኑት የሚገኙት በሶማሌ ክልል መሆኑም ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)