በሀሴት ሀይሉ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ህገወጥ ናቸው” ያላቸውን 471 ሺህ የመሬት ካርታዎችን መሰብሰቡን አስታወቀ። አስተዳደሩ ህገወጥ የሆኑ 260,106 ካሬ ሜትር ይዞታዎችን በመለየት የባለቤትነት መብታቸውን መንጠቁንም ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ ልማት እና አስተዳደር ኃላፊ አቶ ጀማል አልዬ ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 18፣ 2014 ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የመሬት ካርታ በማዕከል የሚሰጥ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ በሚገኙ ክፍለ ከተማዎች አገልግሎቱ ሲሰጥ እንደነበር ተናግረዋል። ይህ አካሄድ ለህገወጥ የመሬት ወረራ መስፋፋት ምክንያት መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል።
“የህገወጥ የመሬት ወረራውን መጠን ለመቀነስ ታሳቢ በማድረግ ህብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት የሚጠቀምበትን ካርታ በአዲስ የመሬት ካርታ ለመለወጥ ዝግጅቶች ተጠናቅቀዋል” ሲሉም የከተማይቱ አስተዳደር በመፍትሔነት ያስቀመጠውን አዲስ አሰራር አሳውቀዋል።
በአዲስ አበባ በመሬት ወረራ ከተያዙት ቦታዎች ውስጥ 260,106 ካሬ ሜትር ያህሉ ተመልሶ ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉን አቶ ጀማል ገልጸዋል። ወደ መሬት ባንክ ከገቡት ይዞታዎች ውስጥ ግንባታ የተካሄደባቸው እንደነበሩ የጠቀሱት ኃላፊው፤ በመሬቶቹ ላይ የተገነቡ ቤቶች እንዲፈርሱ መደረጉን አብራርተዋል።
የዛሬው መግለጫ ከተከታተሉ ጋዜጠኞች “የተሰሩ ቤቶችን ከማፍረስ ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረም ወይ?” የሚል ጥያቄ ቀርቧል። አቶ ጀማል ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “ህግን ከማስከብር በላይ ሌላ አማራጭ የለም” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በነበረው የመሬት ወረራ ብዛት ያላቸው የአስተዳደር እንዲሁም የወረዳ አመራሮች መሳተፋቸው በዛሬው መግለጫ ላይ ተነስቷል። በመሬት ወረራው ላይ ተሳትፎ ነበራቸው ከተባሉ አመራሮች ውስጥ 88 ያህሉ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ልማት እና አስተዳደር ኃላፊ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)