በሃሚድ አወል
በአዲስ አበባ ከተማ ከአትላስ ወደ ካዛንቺስ በሚወስደው መንገድ በጸጋ ሆስፒታል አካባቢ በዛሬው ዕለት የደረሰው የእሳት አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የከተማይቱ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር መስፍን አያሌው፤ አደጋው የደረሰው በውድ የሚገዙ ንብረቶችን በያዙ መጋዘኖች ላይ በመሆኑ ከፍተኛ የንብረት ጉዳት ሳይደርስ እንዳልቀረ በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ዛሬ ሐሙስ ጥር 12 ከቀኑ ስምንት ሰዓት ከሩብ ገደማ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከሁለት ሰዓታት በላይ የቆየ ነበር። አደጋው በደረሰበት ቦታ የሚገኙ ከቆርቆሮ የተሰሩ መጋዘኖች በእሳት አደጋው ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን በስፍራው የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል።
በእሳቱ ለተቃጠሉት መጋዘኖች ቅርብ የሆኑት የተወሰኑ መጋዘኖች በውስጣቸው ያለውን ዕቃ ወደ ወጭ በማውጣት ከአደጋው ለመታደግ ጥረት አድርገዋል። በቦታው መጋዘን ያላቸው ግለሰቦች አደጋው መድረሱን ያለማመን ግርታ ፊታቸው ላይ ይስተዋል ነበር። መጋዘናቸው የተረፈላቸው ግለሰቦች ደግመው ደጋግመው ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ፤ በአደጋው ንብረታቸው የወደመባቸው እና በመጋዘኖቹ ተቀጥረው የሚሰሩ ግለሰቦች በእምባ ሲታጠቡ ታይተዋል።
የእሳት አደጋ በንብረት እስካሁን ግምቱ ያልታወቀ ውድመት ቢያስከትልም፤ በሰው ህይወት ላይ ግን ምንም አይነት ጉዳት አለማድረሱን ምክትል ኮሚሽነሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። የዛሬው የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር 16 ገደማ የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች ተሰማርተው እንደነበር ኮማንደር መስፍን ገልጸዋል። የአዲስ አበባ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን 12 ተሽከርካሪዎቹን በማሰማራት ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥቷል።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሁለት የውሃ ቦቲ መኪናዎቹን፣ የፌደራል ፖሊስ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎቻቸውን ወደ ቃጠሎው ስፍራ በመላክ አደጋውን ለመቆጣጠር ተሳትፎ ማድረጋቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር የአዲስ አበባ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ሰራተኞች፣ የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ርብርብ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ከእሳት አደጋው መከሰት አንድ ሰዓት ገደማ በኋላ በስፍራው የተገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላትም በስፍራው የጸጥታ ቁጥጥር በማድረግ አስተዋጽኦ አድርገዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)