በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ላይ የተጀመረው የእርቅ ሂደት “ተጠያቂነትን ሊያደናቅፍ” እንደማይገባ ኢሰመኮ አሳሰበ

በተስፋለም ወልደየስ

በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ጉዳይ ላይ የተጀመረው የሽምግልና እና የእርቅ ሂደት፤ “የወንጀል ተጠያቂነትን መተካት ወይም ማስተጓጎል የለበትም” ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ። በኦሮሚያ ክልል መንግስት እና በከረዩ ማህበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል እየተካሄደ ባለው በዚህ የእርቅ ሂደት ላይ ቅሬታ ካለ “ከጥቅሙ ይልቅ አሉታዊ ተጽዕኖው ሊያመዝን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ” ኮሚሽኑ አስገንዝቧል።  

ኢሰመኮ ይህን ያለው ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 14፤ 2014 ባወጣው መግለጫ ነው። በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ላይ ያካሄደውን ምርመራ ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ይፋ ያደረገው ኮሚሽኑ፤ ለግድያው ተጠያቂ የሆኑ ተጠርጣሪዎችን ለህግ የማቅረብ ሂደትን አስመልክቶ፤ ከየካቲት 28 ጀምሮ ለስድስት ቀናት ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል። 

ግድያውን ለማጣራት ከኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ መርማሪ ቡድን መቋቋሙን በአዎንታዊ እርምጃነት የጠቀሰው ኢሰመኮ፤ በዚህ ሂደትም ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ማረጋገጡን ገልጿል። ተጠርጣሪዎቹ የሚገኙበትን የማቆያ ቦታ በመጎብኘት ጭምር ያረጋገጠው ኮሚሽኑ፤ በህግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ መሆናቸውን መረዳቱን ገልጿል።

በሂደት የተስተዋሉ ይህን መሰል ጉዳዮች “የተሻለ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ክፍተቶች ናቸው” ሲል ኮሚሽኑ ተችቷል። እስካሁንም በቁጥጥር ስር ካልዋሉ ተጠርጣሪዎች ውስጥ “በተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ” ግለሰቦች ጭምር ያሉ መሆናቸውን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፤ እነዚህ ተጠርጣሪዎች “በምርመራ ሂደቱ ላይ ጫና እያደረሱ ናቸው” ሲል ወንጅሏል። 

ከምርመራ ሂደቱ ጎን ለጎን በኦሮሚያ ክልል የአባገዳዎች ምክር ቤት አስተባባሪነት የሽምግልና እና የእርቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መረዳቱን ኮሚሽኑ ገልጿል። በኦሮሚያ ክልል መንግስት እና በከረዩ ማህበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ይህ ሂደት ግን “የህግ ተጠያቂነትን ሊያደናቀፍ አይገባም” ሲል ኢሰመኮ አሳስቧል። 

“ተጠያቂነትንና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወሰዱ የሕግና የወንጀል ምርመራ እርምጃዎችን በአካባቢዎች ባሕልና ልማድ መሰረት በሚደረጉ የእርቅ ሂደቶች መደገፍ በአንዳንድ ሁኔታዎች የተለመደ ሂደት ቢሆንም፣ የዚህ አይነቱ አሰራር በተጎጂዎች፣ በተጎጂዎች ቤተሰቦችና በአካባቢው ማህበረሰብ ሙሉ ፈቃድና ተሳትፎ ሊሆን ይገባል” ሲል ኮሚሽኑ አጽንኦት ሰጥቷል።

የተጀመረው ሽምግልና እና እርቅ በአካባቢው ማህብረሰብ ዘንድ የህግ ተጠያቂነትን ለመተካት አሊያም ለማስቀረት የሚደረግ መሆኑን የሚያመለክት ቅሬታ ካለ “አሉታዊ ተጽዕኖ” ሊያስከትል ስለሚችል “ከፍተኛ ጥንቃቄ” እንዲደረግ ኮሚሽኑ ምክር ለግሷል። “የተጎዱትን መካስ፣ ዕርቅና ሰላም፣ ፍትሕና ተጠያቂነት በአንድነት ሊተገበሩ የሚችሉና የሚገቡ መሆናቸውን” የጠቀሱት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ ለተሟላ ዕርቅ፣ ሰላምና ፍትህ የመንግስት ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ላይ ግድያ የተፈጸመው ባለፈው ህዳር ወር ነበር። ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ ባደረገው ምርመራ፤ በመንግስት የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ 14 የጅላ አባላት በግዳጅ ወደ ጫካ ቦታ ተወስደው ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ በጥይት ተመትተው እንደተገደሉ ገልጾ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)