የተወካዮች ምክር ቤት የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የቦርድ አባላት ሹመት አፀደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘጠኝ አባላት ያሉትን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የቦርድ አባላትን ሹመት በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ። ምክር ቤቱ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 29፤ 2014 ባካሄደው ስብሰባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሬድዋን ሁሴንን የቦርዱ ሰብሳቢ፤ የቱሪዝም ሚኒስትሯን ናሲሴ ጫሊን ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ አድርጎ ሾሟል። 

የቦርድ አባላቱ ሹመት ከ11 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ሲገጥመው፤ 17 አባላት ደግሞ ድምጽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ 243 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል። 

ባለፈው ዓመት በጸደቀው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በተወካዮች ምክር ቤት የሚሾሙ ዘጠኝ አባላት ይኖሩታል። ቦርዱ የባለስልጣኑን ስራዎች የመቆጣጠር፣ የመገምገም እና ዋና ዳይሬክተሩን በመመልመል ለመንግስት አቅርቦ የማሾም ስልጣኖች በአዋጁ ተሰጥተውታል።

ቦርዱ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ ይግባኞችን የመመልከት እና ውሳኔ የመስጠት ስልጣንም አለው። በአዋጁ መሰረት፤ ቦርዱ ከሲቪክ ማህበረሰብ፣ ከመገናኛ ብዙሃን እና ለመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ጠቀሜታ እና አግባብነት ካላቸው ተቋማት ከእያንዳንዳቸው ሁለት አባላት ይኖሩታል። ቀሪ ሶስቱ አባላት ደግሞ አግባብነት ካላቸው የመንግስት አካላት የተውጣጡ ይሆናሉ። 

ቦርዱ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ ይግባኞችን የመመልከት እና ውሳኔ የመስጠት ስልጣንም አለው። በአዋጁ መሰረት፤ ቦርዱ ከሲቪክ ማህበረሰብ፣ ከመገናኛ ብዙሃን እና ለመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ጠቀሜታ እና አግባብነት ካላቸው ተቋማት ከእያንዳንዳቸው ሁለት አባላት ይኖሩታል። ቀሪ ሶስቱ አባላት ደግሞ አግባብነት ካላቸው የመንግስት አካላት የተውጣጡ ይሆናሉ። 

በሰብሳቢነት እና በምክትል ሰብሳቢነት ከተሾሙት ሁለት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተጨማሪ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባሉ ሀሰን አብዱልቃድርም የቦርዱ አባል ሆነዋል። በመንፈሳዊ አገልግሎቶቻቸው የሚታወቁት ኡስታዝ ያሲን ኑሩ፣ ቀሲስ ታጋይ ታደለ እና ዶ/ር ወዳጄነህ መሃረነ በቦርድ አባላነት ተሹመዋል። 

ቀሪዎቹ ሶስት የቦርዱ አባላት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ናቸው። የስነ ልሳን መምህር የሆኑት ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት ዶ/ር አጋረደች ጀማነህ እና ዶ/ር መሳይ ገብረማርያም የቦርዱ አባላት ሆነዋል። ዶ/ር አጋረደች የአዲስ አበባ ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ መሆናቸው ይታወቃል።

የገዢው የብልጽግና ፓርቲ አባላት በቦርዱ ውስጥ መካተት በፓርላማ አባል እና ጉዳዩን በቅርበት በሚከታተሉ ባለሙያዎች ትችት ቀርቦበታል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የፓርላማ ተወካይ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ የቦርዱ አባላቱ ሹመት “የመገናኛ ብዙሃን አዋጁን የጣሰ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን “የዲሞክራሲ ተቋም የሚባሉትን የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን የመቆጣጠር፣ የመከታተል እና የመደገፍ ኃላፊነት የተጣለበት አንድ ትልቅ የህዝብ ተቋም ነው” ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ “በምን አግባብ ነው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና የገዢው ፓርቲ አባላት ይኼን ዲሞክራሲ ተቋም በቦርድ አመራርነት እንዲመሩ ወደዚህ የቀረቡት?” ሲሉ የቦርድ አባላቱ ሹመት ከመጽደቁ በፊት ተቃውሟቸውን በጥያቄ መልክ ሰንዝረዋል።

የመንግስትን የውሳኔ ሃሳብ በንባብ ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት በፓርላማ የመንግስት ዋና ተጠሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ የቦርድ አባላቱ ሹመት ህግን ተከትሎ የተደረገ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል። “ከመንግስት አካላት የቀረቡ አመራሮችን በተመለከተ አዋጁ ላይ የተቀመጠውን ሃሳብ መነሻ በማድረግ ነው እንጂ የሚጣረስ አይደለም የሚል እምነት አለኝ” ሲሉም አቋማቸውን ለፓርላማ አባላቱ አሳውቀዋል። 

በቦርዱ ውስጥ ያለ ድምጽ በጸሐፊነት የመሳተፍ ስልጣን በአዋጅ የተሰጣቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስም ከመንግስት ተጠሪው ጋር ተመሳሳይ ሀሳብ አላቸው። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር “እነዚህ ሰዎች የመጡት ከመንግስት አካላት ተወክለው ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

አዋጁን በማርቀቁ ሂደት ተሳትፎ የነበራቸው አንድ የህግ ባለሙያ በበኩላቸው፤ በአዋጁ ላይ “የመንግስት ውክልና” በሚል የተጠቀሰው ከገዢው ፓርቲ አባላት ውጭ የሆኑ የመንግስት ኃላፊዎችን ለመጥቀስ የተቀመጠ አገላለጽ ነው ባይ ናቸው። “የመንግስት ውክልና የሚለውን ለመረዳት የሚቸገሩ ሰዎች አሉ። ህጉን ስንቀርጸው፤ ‘የመንግስት ውክልና’ ስንል፤ ‘የፓርቲ አባል ያልሆኑ ሰዎችን’ ማለት ነው” ሲሉም ይሞግታሉ።

በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ላይም የቦርዱ አባል የሚሆኑ ግለሰቦች “የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ ያልሆኑ” መሆን እንዳለባቸው በይፋ ተደንግጓል። “የእኛ ሀሳብ ገለልተኛ ቦርድ እንዲቋቋም ነበር። የገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ ይታይ ስለነበር፣ እነሱን ነገሮች ወደፊት ለማስቀረት የፓርቲ አባል የሆኑ ሰዎችን እንዳይካተቱ አድርገናል” ሲሉ የዛሬው የቦርድ አባላት ሹመት በአዋጁን የተደነገገውን የጣሰ መሆኑን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)